Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሳሚያ ከሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ከብጹዕ አቡነ ዲሜጥሮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሊባኖስ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች እና የመካከለኛው ምስራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጋር በዛሬው እለት ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ብጹዕ አቡነ ዲሜጥሮስ መንግስት በኳታር ላለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና ምዕመናን እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኗ እና ኤምባሲው በኳታር ያሉ ዜጎችን በመርዳት እና በመደገፍ ረገድ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው በመሆኑ በትብብር መስራት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

አያይዘውም በኳታር የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት እያስገነባችው ያለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ከፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እና እስካሁን ሲደረግ የቆየው ሁለገብ ድጋፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብጹዕነታቸው ጠይቀዋል።

አምባሳደር ሳሚያ በበኩላቸው÷ በኳታር የሚኖሩ ዜጎችን በመደገፍ እና በመንግስት በኩል የተለያዩ ሃገራዊ ጥሪዎች ሲቀርቡ ቤተ ክርስቲያኗ የምታደርገውን አስተዋጽኦ አድንቀው በቀጣይም ይኸው ድጋፍ የበለጠ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

ወደፊትም ቤተ ክርስቲያኗ እና ምዕመናን ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎችም ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል በአጽንዖት መግለጻቸውን ኳታር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.