Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና እስራኤል የሳይበር ደህንነት ተቋም ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መከሩ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲና የእስራኤሉ የብሔራዊ ሳይበር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የሳይበር ደህንነት ተቋም ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከእስራኤል መንግሥት የክልላዊና አካባቢ ትብብር ሚኒስቴር ጋር የሁለቱን አገሮች ትብብር ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በዚህም በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለሚገኙ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የበይነ-መረብ የምክክር መድረክ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው፥ የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት የዓለምአቀፍ ትብብር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አብርሃም፣ የሁለቱ አገራት አምባሳደሮችና በሁለቱ አገራት የሳይበር ደህንነት ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡

በውይይቱ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ረታ አለሙ የትብብር ማዕቀፉ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ለተግባራዊነቱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የእስራኤል መንግሥት ዝግጁ መሆኑንና ለዚህም በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ዕቅድ መሠረት እንዲጀመር አመልክተዋል፡፡

ተቋማቱ በጋራ ለመሥራት የሚፈጠረውን የትብብር ማዕቀፍ በሚመለከት በቀረቡ ሀሳቦች፣ በዋናነት በዘርፉ የሰው ሐይል ሥልጠና፣ በሁለቱም አገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የሳይበር ደህንነት የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር እና የዘርፉን የምርምር ተቋም ማቋቋም በሚመለከት ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ዙርያ ምክክር የተደረገ ሲሆን፥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ረቂቅ የመግባቢያ ስምምነት በአጭር ጊዜ ለመፈራረም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.