በብራዚል ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ እና መሬት መንሸራተት አደጋ የ30 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብራዚል ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የ30 ሰዎች ህይዎት ማለፉ ተነገረ።
በሚናስ ጌራይስ ግዛት መዲና በጣለው ከባድ ዝናብ ከሞቱት በተጨማሪ 17 ሰዎች የገቡበት አለመታወቁን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አስታውቀዋል።
በ24 ሰዓት ውስጥ የተመዘገበው የዝናብ መጠን፥ በሃገሪቱ ከባድ የዝናብ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመዘገበበት 110 አመት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
በጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋው ሳቢያ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውም ነው የተነገረው።
የነብስ አደን ሰራተኞችም በህይዎት የተረፉ ሰዎችን ማፈላለጋቸውን ቀጥለዋል።
የአሁኑ አደጋ ከመዲናዋ አቅራቢያ የተከሰተውና የ270 ሰዎች ህይዎት ያለፈበት የግድብ መደርመስ አደጋ መታሰቢያ እየተከበረ ባለበት ወቅት የደረሰ ነው።
ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ