Fana: At a Speed of Life!

ህወሃት አካባቢውን ወደ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እያስተጓጎለ ነው – አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሃት አካባቢውን ወደ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በጂቡቲ ከአሜሪካ አምባሳደር ጆናታን ፕራት ጋር በወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በትግራይ ክልል የተደረሰውን የተናጥል የተኩስ አቁም በማስታወስ፥ መንግስት አርሶ አደሩ የክረምቱን ወቅት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠቀም በማሰብ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ለአምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም መንግስት የኤርትራን ወታደር ከኢትዮጵያ ድንበር ማስወጣቱን በመጥቀስ፥ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረስ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጅ ህወሃት ከዚህ በተቃራኒው አሁንም የሚፈጽመውን ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እንደቀጠለበትና አካባቢውን ወደ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ብርሃኑ አያይዘውም ባለፈው ሰኔ 14 ቀን የተካሄደው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ግልጽና ታማኝነት ባለው መልኩ መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት ሲቪክ ማህበራት፣ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና ፍርድ ቤቶችም የምርጫውን ሂደት መታዘባቸውን አንስተዋል፡፡

የአሜሪካው አምባሳደር ጆናታን ፕራት በበበኩላቸው ምርጫው በተሳካ ሁኔታ በመካሄዱ እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው የኢትዮ ጂቡቲን የሁለትዮሽ ግንኙነት አድንቀዋል፡፡

አምባሳደሮቹ በውይይታቸው ወቅት በሁለቱ ሃገራት የጋራ ጉዳዮች በሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.