Fana: At a Speed of Life!

ለሰራዊታችን የምናደርገውን ማንኛውንም ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
ሙሉ የአቋም መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ኢትዮጵያን የማፍረስ ቅዠት በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር ይመክናል!
በሰሜን ኢትዮጲያ ከተካሄደዉ የህግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ መንግስት ህዝቡ በጦር እንቅስቃሴ ሳይረበሽ በጥሞና ጊዜ ፋታ አግኝቶ እርሻውን የሚያከናውንበት የእርዳታና ድጋፍ አቅርቦቱም ያለሰበብ ሳይደናቀፍ የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ወስዷል፡፡
ሆኖም ግን ይህ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ መንግስት የታወጀውን ህዝብን ያስቀደመ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ተጠቅሞ ከስህተቱ ተምሮ የትግራይን ህዝብ ከከፋ ስቃይ እና መከራ መታደግ ሲገባው፤ የመንግስትን አርቆ አስተዋይነት እንደሽንፈት ቆጥሮ ከተደበቀበት ጎሬ ወጥቶ እንደ ድል አድራጊ በየአካበቢው መፎከር ብቻ ሳይሆን ከዚያም አልፎ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም የተዘረጉትን መልካም የሰላም እድሎችን ሁሉ ዝግ በማድረግ እንደገና ጥቃት ከፍቷል፡፡
ጥቃቱ የተከፈተብን መላ ኢትዮጵያውያን አለምን ባስደነቀ መልኩ እጅግ ሰላማዊ የሆነ ምርጫ አከናውነን የጋራ አሸናፊነታችንን ባረጋገጥንበት ለዲሞክራሲ ግንባታ ያላንን ቁርጠኝነት በተግባር ባሳየንበት ወቅት መሆኑም ብቻ ሳይሆን ሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብን በመሙላት ላይ ባለንበትና መላው ኢትዮጵያውያን የሃገራችንን የትንሳኤ ዘመን ብስራት የሆነው የህዳሴ ግድባችን ላይ እየተቃጣ ያለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ለሉአላዊነታችን መከበር በአንድነት ትከሻ ለትከሻ በቆምንበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን በተለየ ስሜት እንድንመለከተውና ሃላፊነታችን ላቅ ያለ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡
ይህ የሽብር ቡድን ለዚህ እኩይ አላማው፤ እንክብካቤ የሚያሻቸው ፤የጦር መሳርያ ሳይሆን ደብተር ማንገብ የሚገባቸውን ህፃናት፤ የሃይማኖት አባቶችን ፤አዛውንቶችን ደካሞችን ጨምሮ በግዳጅ በጦርነት በመማገድ ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፍ ህግጋት ተፈጻሚነት ደንታ የሌለው ጨካኝ ቡድን መሆኑን በይፋ እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎቻቸዉ ጭምር ይህ የሽብር ቡድን መንግስት ተግባራዊ ያደረገዉን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ወደ ጎን በማለት በንጹሀን ላይ እምነትን ጭምር መሰረት አድርጎ ግድያና ጭፍጨፋ ሲያካሂድ፤ባለዉ አቅም ሁሉ ትንኮሳ ከማድረግ አልፎ ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጅና ሲጀምር የተቋቋሙበትን ዋና ዓላማ እና የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር በጣሰ መልኩ ጉዳዩን አይቶ እንዳላየ ሲያልፉት ተመልክተናል፡፡ ይባስ ብለዉ አሁን ላይ መንግስት የህልዉና ዘመቻዉን በጀመረበት ሰዓት የተኩስ አቁም ይደረግ በሚል የተለመደ የሽብር ቡድኑን የማዳኛ ታክቲካቸዉን ለመተግበር ሲሯሯጡ ታዝበናል፤ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ተግባር ለመላዉ የኢትዮጰያ ህዝብ ድብቅ አላማቸዉን ይፋ ያደረገ ሆኗል፡፡
ወትሮም ቢሆን እኛ ያልመራናት ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ማደር የለባትም
‘’እኔ ከሞትኩ፤ ሰርዶ አይብቀል’’ እንዲሉ በተደጋጋሚ እኔ ካልመራዉ ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት! በማለት ሲናገር የከረመውና ላለፉት አመታት አቅሙ በቻለው ሁሉ ከውስጥም ከውጪም ካሉ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ሁሉ ጋር ሲሰራና ሲያሰማራ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን ሲያደርግ የቆየው ይህ ቡድን ከጥፋት ተልእኮው መቼም የማይመለስ መሆኑ ለማንም ተመልካች ግልፅ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን የተጀመረው ማጥቃት እና ትንኮሳ፤ የአንድ ወገን የአንድ አካባቢ ጥቃት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ጥቃት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ ፤ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የገፋው በህልውናችን ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን የሃገራችን ህዝቦች መተባበርና አንድነት እንቅልፍ የሚነሳው፤ ኢትዮጵያ ተበታትና እስካላየ አልያም እራሱ እስካልመራ ድረስ መቼም ቢሆን አርፎ የማይቀመጥ፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በተግባር ያረጋገጠ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ጠላት ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሁልጊዜውም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ በሆነው ሰራዊታችን ኩራት ይሰማናል፡፡
ለሰራዊታችንም ማንኛውንም ድጋፍ ማድረግን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
በዚህ ሰአት አሸባሪ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት በመመከት የተጀመረው ሃገር የማዳን ተልእኮ ግቡን እንዲመታ መላው ህዝባችን ለሃገሩና ለሰራዊቱ ሁሌም እንደሚያደርገው ያልተቆጠበ ሁለንተናዊ ድጋፍ በገንዘብ፤ በጉልበትም ሆነ በዕውቀት አቅም በፈቀደው ሁሉ በማድረግ ሃገራዊ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
ወጣቶችና አቅማችን የሚፈቅድ ሰራዊታችንን በመቀላቀል ፤ሌሎቻችን ደግሞ የሞራልና የስንቅ ድጋፋችንን አጠናክረን በመቀጠል ደጀንነታችንን በተግባር የምናሳይበት መሆን ይኖርበታል፡፡
መላው ኢትዮጵያውን፤ በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሸባሪው ቡድን በሚነዙ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ሳንወናበድ፤ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር፤ እርስበእርስ በመመካከርና በመደጋገፍ፤ የተቃጣብንን አገራዊ ጥቃት በህብረትና በአንድነት፤ እንደ አንድ ልብ ሆነን ልንመክት ይገባል፡፡
በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ የፀጥታ ሀይሉን በጋራ በትብብር በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስምሪትና ተግባር የምትተቹና እየከፋፈላቹህ በማህበራዊ ሚዲያ የምትፅፉ ከዚህ ድርጊታቹህ በመቆጠብ ይልቁንም የፀጥታ ሀይሉን ስምሪት ለፀጥታ አካሉ ትተን፤ በሀገራችን ላይ ከውስጥም ከውጭም በየአቅጣጫው የተከፈተውን የዲጂታል ሚዲያ ጦርነት በትብብርና በአንድነት ልንመክት ይገባል፡፡
የከተማችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች ለሰራዊታችን ከምናደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍም ባሻገር የአካባቢያችንን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ፤ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በትብብርና በቅርበት በመስራት፤ ለህዳሴ ግድባችን ድጋፋችንን በማጠናከር ፤ የጀመርነውን የከተማችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ እንቅስቃሴ እንቀጥላለን፤ አገራዊ ሃላፊነታችንን በንቃት እንወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!!
ጀግኖች አባቶቻችን ተባብረውና ተጋግዘው በጀግንነት ያቆዩልንን ነፃ ሃገር እኛ ልጆቻቸው የአባቶቻችንን ታሪክ በመድገም የኢትዮጵያን ክብር ከፍ እናደርጋለን!
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ህብረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!
ሃምሌ 2013
አዲስ አበባ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.