በአይቮሪ ኮስት የኮሮና ቫይረስ ምልክት ታይቶባታል የተባለች ሴት ምርመራ እየተደረገላት ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአይቮሪ ኮስት ኮሮና ቫይረስ ታይቶባታል የተባለች ሴት ምርመራ እየተደረገላት መሆኑን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ምርመራው ከአዲሱ ቫይረስ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ የጉንፋን አይነት ምልክት መታየቱን ተከትሎ ነው እየተደረገ ያለው።
በተደረገላት ምርመራ ከቫይረሱ ጋር ሊዛመድ ይችላል የተባለ የሳንባ ምች ምልክት ታይቶባታልም ነው የተባለው።
የ34 አመቷ ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በማቆያ ክፍል ብቻዋን እንድትሆን መደረጉን የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች ተናግረዋል።
በቤጂንግ ትምህርቷን ትከታተላለች የተባለችው ግለሰብ ክትትል እየተደረገላት ሲሆን፥ ቫይረሱ ከተገኘባት በአህጉሪቱ የመጀመሪያው ይሆናልም ነው የተባለው።
በቻይና ውሃን የተቀሰቀሰው ኮሮና ቫይረስ ምክንያት እስካሁን 81 ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ምንጭ፦ ቢቢሲ