Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግን ዓለም አቀፍ ጫና የሚቃወም የትዊተር ዘመቻ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጫናዎችን እና ጣልቃ ገብነቶችን በመቃወም እንዲሁም ህፃናትን ለውትድርና እየተጠቀመ ባለው የህወሓት ቡድን ላይ ጫና እንዲደረግ የሚጠይቅ የትዊተር ዘመቻ አካሄዱ፡፡

የትዊተር ዘመቻው በተለይም አሸባሪው ሕወሓት እያደረገ ያለውን ትንኮሳ እና ህጻናትን ለውትድርና መጠቀሙ የህጻናት መብቶችን እና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጣረስ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው የሚጠይቅ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ቡድኑ እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ትንኮሳ በአስቸኳይ ያቆም ዘንድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳድርም የጠየቀ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በትግራይ ስላለው ግጭት እያቀረቡት ያለው መረጃ በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ መሆኑንም የዘመቻው ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

አሜሪካም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የያዘችው አቋምና በውስጥ ጉዳይ ላይ እያደረገች ያለው ጣልቃ ገብነት አግባብነት የሌለውና አሸባሪውን ቡድን የሚደግፍ ነው በሚል የዘመቻው ተሳታፊዎች ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም የተዛባ ብሎም ምዕራባውያን አሸባሪው ህወሓት ከፊት ለጦርነት ያሰለፋቸው ህፃናት ጉዳይ ግድ ሳይሰጣቸው ባለየ ማለፋቸው ተገቢነት እንደሌለውም ነው ተሳታፊዎቹ የገለጹት፡፡

በዘመቻው የሽብር ቡድኑ በመከላያ ሰራዊት እና በማይካድራ የፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋን በማስታወስ ምዕራባውያን ይህን መዘንጋታቸው እንዳሳዘናቸውም አመላክተዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሃገራት የኢትዮጵያን ጉዳይ በፍትሃዊነት እንዲያጤኑት እና ሉዓላዊነቷን እንዲያከብሩም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.