Fana: At a Speed of Life!

ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው ለተለዩ 520 ሺህ ዜጎች ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተይዟል–የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው ክረምት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው ለተለዩ 520 ሺህ ዜጎች ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መያዙን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ክረምት  ከገባ ጀምሮ   በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ዝናብ እንደሚያገኙ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል።

በተለይ በምዕራብ አጋማሽ የሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች በክረምት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ያገኛሉ፡፡

ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተገልጿል።

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ደረጀ ጌታነህ ለኢዜአ እንዳሉት÷ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመከላከል በተደረገው የቅድመ ማጣራት ተግባር 520 ሺህ ዜጎች ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ተለይተዋል።

በመሆኑም የጎርፍ አደጋ በዜጎች ህይወትና ንብረት ጉዳት እንዳያደርስ የቅደመ መከላከል ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

የጎርፍ አደጋው በሁሉም ክልሎች የሚከሰት ቢሆንም በአብዛኛው በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሱማሌ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች እንደሚጠቁሙ አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡

አደጋው በሀገር አቀፍ ደረጃ በ246 አካባቢዎች ሊከሰት እንደሚችል መለየቱን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 64 ወረዳዎች ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በደቡብ ክልል 52 ወረዳዎች፤ በአማራ ደግሞ 27 ወረዳዎች ላይ አደጋው ሊከሰት እንደሚችልም ጨምረው ገልጸዋል።

አደጋውን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላትና ከህዝቡ ጋር በመተባበር የወንዝ ዳርቻዎችን የመገደብ ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል።

ከግድቦች የሚለቀቅ ውሃ በአካባቢው ጉዳት በማያደርስ መልኩ አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲከናወን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የገለጹት።

የአደጋ መከላከልና ማስጠንቀቂያ መረጃና የግንዛቤ ማስጨበጫ ለአደጋው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ለተለዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች እንደተሰጠም አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡

ጀልባዎችን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል፡፡

በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለሚደርስባቸው ዜጎች የምግብ፣ አልባሳትና ቁሳቁስ ለማቅረብ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ  በጀት መያዙንም ገልፀዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የጎርፍ ማፋሰሻ ቱቦዎች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው ÷ አርሶ አደሩም በእርሻ ማሳዎች የውሃ ማፋሰሻዎችን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበት መክረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን በዘላቂነት ምቹ በሆኑ ቦታዎች ለማስፈር ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.