Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈፀመ ባለው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ትዴፓ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት አሸባሪ ቡድን ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈፀመ ባለው ከባድ ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ጥሪ አቀረበ።
የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ንጉሴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ህፃናትን ለጦርነት ማሰለፍ በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም ህግ በከባድ ወንጀል ያስጠይቃል።
የህወሓት አሸባሪ ቡድን ይህንን ህግ በመተላለፍ ህፃናትን በመመልመል ለጦርነት በማሰለፍ ወንጀል በመፈፀም ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ቡድኑ እየፈፀመ ባለው ከባድ ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ብለዋል አቶ ተሻለ።
የህወሓት የጥፋት ቡድን የተለያዩ ወንጀሎችን የመፈፀምና አገር የማፍረስ ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ያስታወሱት የትዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሁን ላይ ደግሞ ህፃናትን ወደ ጦርነት መማገዱን ተያይዞታል ብለዋል።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሃትን ቡድን በዓለም አቀፍ ህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የትግራይ ሕዝብም ምንም አይነት አላማና ምክንያት አልባ በሆነ ጦርነት ሕፃናት ልጆቹን ማጣት ስለሌለበት የቡድኑን እኩይ አላማ መቃወምና ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በተለይ የግብረሰናይ ድርጅቶች የሽብር ቡድኑ በሕፃናት ላይ የሚያደርሰውን ወንጀል እያዩ ዝምታን መምረጣቸው የሚያሳዝን ነው ብለዋል።
በአሸባሪ ቡድኑ ተግባር መላው ሕዝብ ጉዳት የሚደርስበት ቢሆንም በተለይ የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ በመሆኑ እንዲታገለው አቶ ተሻለ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ልጆችና ቤተሰቦቹን በውጭ አገራት እያኖረ የድሃ ልጆችን ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ ሊቀበለው አይገባም ነው ያሉት።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ የህወሓት የሽብር ቡድን በህፃናት ላይ እየፈፀመ ያለውን ወንጀል በመቃወም በቅርቡ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጣም አቶ ተሻለ ጠቁመዋል።
በተባበሩት መንግሰታት የህፃናት መብት ኮንቬንሽን አንቀፅ 38 እንደተመለከተው ህፃናት ለጦርነት ያለመመልመል፣ ያለመሳተፍ እና የመሳሰሉት መብቶች አሏቸው፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.