በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ ቻይና የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
እስከ ዛሬ ባለው መረጃ በቻይና በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ኤምባሲውን ጠቅሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
በተለይም የኮሮና ቫይረስ በተቀሰቀሰባት ሁቤይ ግዛት መዲና ውሃን ከተማ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፥ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው እና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኤምባሲው እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከቻይና ውጭ በተለያዩ ሃገራት እንደተከሰተ መረጋገጡን ከጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።