ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ትብብሯን በማጠናከር የመከላከያ ኃይሏን ማዘመን ትፈልጋለች- አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር በማጠናከር የመከላከያ ኃይሏን ማዘመኗን መቀጠል እንደምትፈልግ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ገለፁ።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ትብብር በማጠናከር የመከላከያ ሰራዊቷን በተለይ ሰላም በማስከበር እና ሽብርን በመከላከል ተግባር ላይ ጦሯን ማዘመን እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
ሀገራቱ በመከላከያ ትብብር ዙሪያ ከዚህ ቀደም ስኬታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ፥ በፈረንጆቹ ህዳር ወር ላይም ቀጣይ ውይይት እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ በአካባቢው ጠንካራ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ፥ በሰላም ማስከበር እና ሽብርተኝነትን በመከላከል ላይ የሚሰራቸውን ስራዎች አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የወታደራዊ ዘርፍ የሁለትዮሽ ውይይታቸውን ባለፈው የፈረንጆቹ ህዳር ወር ላይ አድርገዋል።
በሩሲያ የተካሄደው የመከላከያ ትብብር የሁለትዮሽ ስብሰባ ስኬታማና በበርካታ ጉዳዮች ስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆን በመግለፅ ተመሳሳይ ውይይት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
የሁለትዮሽ ስብሰባው በተካሄደበት ህዳር ወርም ኢትዮጵያ ከሩሲያ የሸመተችውን ፓንትሲር ኤስ 1 የአየር መከላከያ የሚሳኤል ስርዓት ከሞስኮ መረከቧን ስፑትኒክ ዘግቧል።