Fana: At a Speed of Life!

በሶስት የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሙስና ተጋላጭነት መታየቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በመሬት አስተዳዳር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም የግንባታ ዘርፎች ላይ አሁንም ከፍተኛ የሙስና ተጋላጭነት መኖሩን አንድ ጥናት አመለከተ።

የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን 3ኛው ሃገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናትና የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

ጥናቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የሃገሪቷ ክልሎች ከተለያዩ የህይወት መስክ ላይ የሚገኙ 6 ሺህ 627 ሰዎችን አካቷል።

ጥናቱንም ‘ፍሮንቴር’ የተሰኘ የጥናት ተቋም 130 ባለሙያዎች መድቦ አካሂዶታል።

የጥናቱ ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ሃብታሙ ወንድሙ እንደተናገሩት ጥናቱ በሃገሪቷ አሁን ላይ ያለውን የሙስና ደረጃ አመለካከት አሳይቷል።

በዚህም መሰረት ሙስናን ማጥፋት ለእድገትና ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ በመሆኑ የሙስና መከላከል ተግባር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጥናቱ መጠቆሙን ተናግረዋል።

የጥናቱ ውጤትም በአሁኑ ወቅት ሃገሪቷን ከሚፈትኑ ትላልቅ ችግሮች መካከል ሙስና በሶስተኛ ደረጃ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተለይም ደግሞ በሃገሪቷ በመሬት አስተዳዳር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ግንባታ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሙስና ተጋላጭነት አለ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች አካባቢም ታጋላጭነት መኖሩን ጠቁመዋል።
ስለዚህም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ መቀየስ እንደሚገባቸው ጥናቱ ማመልከቱን ነው የተናገሩት።

የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በበኩላቸው “ኮሚሽኑ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ወጥ ለማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.