Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ከ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሃብት ላይ ጉዳት ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ከ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሃብት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ 12 ወራት ውስጥ 62 ግጭቶች በቀለበት መንገድ በሚገኙ ሃብቶች ላይ ሲደርስ ÷ 310 ግጭቶች ደግሞ ከቀለበት መንገድ ውጪ በድምሩ 372 የሚሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ከፍተኛ የሀገር ሃብት ፈሶባቸው በተገነቡ የመንገድ አውታሮች ላይ በየጊዜው በተሸከርካሪዎች ግጭት እየደረሰ ያለው ጉዳት በአጠቃላይ የትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባለፈ የሀገርን ኢኮኖሚ ለኪሳራ እየዳረገ ነው፡፡
ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙት የመንገድ ሃብቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ በተተከሉት የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦችና የውሃ መውረጃ ቱቦዎች እና ክዳኖች ላይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መንገዶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ስለሚኖርበት ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ ጉዳት አድራሾቹ ሙሉ በሙሉ እንዲከፍሉ ማድረጉን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በአግባቡ ለማሳለጥ እና የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል መንገዶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመንገድ ሀብቶችን ከጉዳት በመጠበቅና በመንከባከብ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.