Fana: At a Speed of Life!

በናይጀሪያ በላሳ ትኩሳት ወረርሽኝ 29 ሰዎች ለህልፈት ተዳረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በናይጀሪያ በተከሰተ የላሳ ትኩሳት ወረርሽኝ በትንሹ የ29 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የሀገሪቱ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት በተያዘው የፈረንጆቹ ጥር ወር በወረርሽኙ ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ 195 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውን ገልጸዋል።

የሀገሪቱ በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል በበኩሉ፥ የላሳ ትኩሳት ወረርሽኝ በ11 የሀገሪቱ ግዛቶች መስፋፋቱን አስታውቋል።

በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ ዘመቻ ማዕከል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

የላሳ ወረርሽኝ በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ሲሆን፥ ከኢቦላ እና ማርቡርግ ቫይረስ አምጭ ተህዋስያን ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ወረርሽኙ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው በሚወጣ ፈሳሽ፣ ንክኪ እና የግብረ ስጋ ግንኙነት ይተላለፋል።

ከዚህ ባለፈም ንጽህናቸው ያልተረጋገጠ እና የቫይረሱ ተጠቂዎች የተጠቀሙባቸውን እቃዎች በመገልገል ይተላለፋልም ነው የተባለው።

ላሳ ትኩሳት በፈረንጆቹ 1969 ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየባት የናይጀሪያዋ ላሳ ከተማ ስያሜውን ማግኘቱ ይነገራል።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.