Fana: At a Speed of Life!

ነባር የስኳር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት በመጀመራቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ነባር የስኳር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በመደረጉ ውጤታማ እንዳደረጋቸው የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዩ ሮባ ፋብሪካዎቹ ቀደም ሲል በተቀመጠላቸው መጠንና ጥራት ልክ እያመረቱ እንዳልነበረ ተናግረዋል።

የአደረጃጀት ችግር፣ ቋሚ የጥገናና የስራ ጊዜ ተለይቶ አለመተግበርና ሌሎች ችግሮችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ፋብሪካዎቹ ስራ ከጀመሩ በኋላ ለጥገና ስለሚቆሙና ለዚህም የማካካሻ አሰራር ስላልነበራቸው ከታቀደላቸው የምርት መጠን በአማካይ በግማሽ ሲያመርቱ ቆይተዋል ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በነባር ፋብሪካዎች አሰራር ላይ በተደረገው ለውጥ ችግሮቹ በመቃለላቸው የምርት መጠናቸው በዕጥፍ እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘርፉ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ማግኘት አለመቻሉም በውጤታማነቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንም አስረድተዋል።

አሁን ላይም ለዘርፉ በቀጥታ ተግባር ላይ የሚውሉ የትምህርት ሙያዎችን በመለየት ስርዓተ ትምህርት እንዲቀረፅና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጋር በመዋዋል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የተማሩና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ማፍራት ተጀምሯልም ነው ያሉት።

አሁን ላይ ላይ ለፋብሪካዎቹ በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች ጥገና መደረግ መጀመሩን ተከትሎም ለውጭ ኩባንያዎች ለጥገና የሚወጣውን ገንዘብ ማዳን ተችሏል ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.