Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በጅምር የቀሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በጅምር የቀሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ስራ ፈጠራ እና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ከክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት ጀምሯል።

ማስተባበሪያው የፕሮጀክቶቹን ችግር በመለየት በ8 ሳምንታት ውስጥ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ዘዴን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል።

በክልሉ ከአጠቃላይ የግሉ ኢንቨስትመንት 57 በመቶ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በጅምር የቀሩ መሆናቸውን ከማስተባበሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል 22 በመቶዎቹ በግንባታ ሂደት እና 44 በመቶዎቹ ደግሞ ግንባታ አጠናቀው በጥቃቅን ችግሮች ምክንያት ወደ ተግባር አለመግባታቸው ነው የተነገረው።

ውዝፍ የዘርፉ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ለመስጠት የቢኤፍ አር ስነ ዘዴን ለመጠቀም ስራዎች መጀመራቸውን የፕሮጀክቱ አማካሪ እና የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዶክተር ደጉ ሰጠኝ ተናግረዋል።

መፍትሄው ሳይንሳዊ መሆኑን የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፥ ተሞክሮው በማሌዥያ የግል ፕሮጀክቶችን ወደ ትርፋማነት መመለሱን ጠቁመዋል።

በክልሉ የግሉ ዘርፍ ለ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ቢጠበቅም ለ540 ሺህ ዜጎች ብቻ የስራ እድል መፍጠሩንም ገልፀዋል።

ከሶስት ሳምንታት በፊት የተጀመረው የመፍትሄ ማፈላለጊያ እቅድ በግብርና፣ በማምረቻው፣ ቱሪዝምና በማዕድን ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶችን ያሳተፈ ነው ተብሏል።

ባለሀብቶች በሰጡት አስተያየት የክልሉ መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀው፥ የድጋፍና የክትትል ስራው አነስተኛ መሆኑንም አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ስራ ፈጠራ እና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ሀላፊ አቶ ሁንዴ ዱጋሳ እንደተናገሩት የመፍትሄ ማፈላለጊያ እቅዱ ችግሩን በመለየት ፈጣን መፍትሄ በአጭር ጊዜ ማስቀመጥ በመሆኑ ከባለሀብቶቹ ጋር በተከታታይ በሚደረግ ውይይት ከመንግስት የሚጠበቀው እርምጃ ይወሰዳል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.