Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ህጻናትን በጦር ግንባር ማሰለፉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ደንታ እንደሌለው ማሳያ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት ቡድን ህጻናትን በጦር ግንባር ማሰለፉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ደንታ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ህወሓት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፎችን በማስተጓጎል ጥሰት እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ቡድኑ በጦር ግንባር ህጻናትን እያሰለፈ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለሰብአዊ መብቶች መከበር ደንታ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ቢያውጅም ህወሓት ይህን ውሳኔ አለማክበሩን ጠቅሰው፥ የቡድኑ ድርጊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዲረዳና ጁንታውን እርቃኑን ያስቀረው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘም አንዳንድ ዓለም አቀፍ አካላት የመንግስትን አቋም መረዳትና መቀበል ተስኗቸዋልም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡

ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡

የውሃ ሙሌቱ የህዳሴ ግድብ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ከሙሌቱ ጋር ተያይዞም በሶስትዮሽ ድርድሩ መሰረት ለሁሉም ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች ደብዳቤ እንዲደርስ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

በመግለጫው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደስታ መልዕክት መላካቸውን ገልጸዋል።

በፖለቲካዊ መስክም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብና የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ገለፃ መደረጉን አንስተዋል።

በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ጫና ተገቢ አለመሆኑን ለልዩ ተወካዩ ገለጻ መደረጉንም ነው የገለጹት።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ኬኒያ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ከየሃገራቱ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ዲና መንግስት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ አሁንም ጠንካራ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን አንስተው፥ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችም ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከተመላሽ ዜጎች ጋር በተያያዘም ከሳዑዲ አረቢያ ከ130 በላይ በረራዎችን በማድረግ ከ41 ሺህ በላይ ዜጎች መመለሳቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.