Fana: At a Speed of Life!

በሃረሪ ክልል ኮቪድ19 ለመከላከል አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎች የምስጋና እና የዕውቅና መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል በምርመራ የኮቪድ19 ከተከሰተበት ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ላገለገሉ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በእውቅና ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ቅድመ ዝግጅት እስከ ምላሽ አሰጣጥ ከፍተኛ ሚና ላበረከቱ አካላት የእውቅና ምስክር ወረቀት የሰጡት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በኮቪድ19 መከላከለል ስራ ላይ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች የሌሎችን ህይወት ለማዳን ሲሉ ህይወታቸውን ሰጥተዋልና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

ጀግንነት ሁልጊዜ በጦርነት ብቻ ባለመሆኑና የጤና ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ከሞት ጋር ያደረጉት ትግል ሁልጊዜም በልባችን ይኖራልም ነው ያሉት።

የቫይረሱ ስርጭት አሁንም ያልተገታና ከስጋት ነፃ ስላልሆነ እንዲሁም ባህሪውን በየጊዜው እየቀያየረ በመሆኑ እንደ ከዚህቀደሙ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ኦርዲን አሳስበዋል።

የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም በበኩላቸው፥ የኮቪድ19 ስርጭትን ለመከላከል ከጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋቸውን አቅርበዋል።

ቫይረሱ በክልሉ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ከ55ሺህ በላይ የላቦራቶሪ ምርመራ መደረጉን፣ በ4 ሺህ 345 ሠዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱንና እስከ ዛሬ ድረስ 134 ሠዎች በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውቀዋል።

በተሾመ ኃይሉ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.