የሀገር ውስጥ ዜና

መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር በአንድነት መሰለፉ ጊዜዉ የሚጠይቀዉ ተግባር ነው – አቶ ዕርስቱ ይረዳ

By Meseret Awoke

July 22, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር በአንድነት መሰለፉ ጊዜዉ የሚጠይቀዉ ተግባር መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዕርስቱ ይረዳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት ክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ ልዩ ሀይሉን ወደ ግዳጅ ቀጠና ለመላክ ሽኝት በሚያደርግበት ጊዜ ነዉ፡፡

አቶ እርስቱ የኢትዮጵያን እድገትና ሰላምን የማይፈልጉ አገሪቷ ላይ ጫናን ያበረከቱ አካላት ቢበዙም ይህንን ጫናም እያለፍን ነዉ ብለዋል፡፡

የአሸባሪዉ የህወሃት ጁንታ ቡድን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስደፈር የሚሰራዉን ስራ ኢትዮጵያዊን በጋራ በመሆን መከላከል እንደሚኖርባቸዉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ የተናጠል ተኩስ አቁም ቢወስድም አሸባሪ ሀይሉ በድጋሚ ለማንሰራራት እየተዉተረተረ ይገኛልም ነዉ ያሉት፡፡

ስለዚህ ይህንኑ ሀገራዊ መከታነታቸዉን ለማሳየት ይችሉ ዘንድ የክልሉን ልዩ ሀይል ለ2ኛ ጊዜ ወደ ግዳጅ እየተላከ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን ላለማስደፈር የጠላትን ሴራ በማምከን ድልን እንቀዳጃለን ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉ ህዝብ ለመከላከያ አስፈላጊዉን ቁሳቁስ፣ የገንዘብ ድጋፍና ስንቅ በማዘጋጀት የተጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ ልዩ ሀይል ለግዳጅ እንዲሰማራ ከተጠየቀ ክልሉ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊዉ አቶ አለማየሁ ባዉዲ በበኩላቸዉ፥ ልዩ ሀይሉ በሙያዊ ስነምግባር ግዳጁን እንደሚወጣ እምነቴ ነዉ ብለዋል፡፡

የልዩ ሀይል አባላቱ የሃገራዊ ጥሪዉን በመቀበል የአገርን ሰላም ለሚያፈርሱ አካላትን የሚገባቸዉን ቅጣት ለመስጠት ቆርጠዉ መነሳታቸዉን ገልጸዋል፡፡

በሀይማኖት ወንዲራድ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!