የሀገር ውስጥ ዜና

በዱር በገደሉ ተጋድሎ ለሚያደርገው ሰራዊት ደም መለገስ ለነገ የሚባል አይደለም – የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች

By Tibebu Kebede

July 24, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም ይገባ ዘንድ ሠራዊታችን በዱር በገደሉ ለሚያደርገው ተጋድሎ ደም መለገስ ለነገ የማይባል ተግባር ነው አሉ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች፡፡

የደም ልገሳ መርኃግብሩን የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶችና ወጣቶች ሊግ አደረጃጀት ከጎንደር ደም ባንክ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት፡፡

የዞኑ ወጣቶች ሊግ ምክትል አስተባባሪ ገብረእግዚአብሔር ሙላው ሠራዊቱ አሸባሪው ትህነግ ለመደምሰስ እያደረገ ያለውን ትግል ማኅበረሰቡ በቁሳቁስ፣ በስንቅና በገንዘብ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ደም በመለገስ ደጀን መሆኑን አስቀጥሏል ብለዋል፡፡

የጎንደር ደም ባንክ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደመቀ ጥላሁን አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ በመደገፍ ሁሉም በሚችለው እያገዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ደም ባንክ አገልግሎትም ከማኅበረሰቡ ደም የመሰብሰብ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡

በደባርቅ ከተማ ለሁለት ቀን በሚደረገው የደም ልገሳ መርኃ ግብር ከ300 ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አሚኮ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!