Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የክተት ጥሪ አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በመንግስትም ሆነ በግላቸው መሳሪያ የታጠቁ ሁሉ የአሸባሪው ህወሓት ጁንታን ለመመከት የታወጀውን የሕልውና ዘመቻ እንዲቀላቀሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የክተት ጥሪ አስተላለፉ።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሸባሪው ትህነግ በተለያዩ ግንባሮች ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ የማጥቃት ሙከራ እያደረገ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ከጎናችን እንዲሆን ባስተላለፍነው መልዕክት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ረገድ ከጎናችን ሆኗል ነው ያሉት።
ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና ይገባዋልም ብለዋል።
የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ለክልሉ መንግሥትና ለጸጥታው ኃይል ያደረጉት ድጋፍ የክልሉን መንግሥት አኩርቷል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ባለሀብቶችና የንግዱ ማኅበረሰብ እያደረጉት ላለው ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ ሕዝብና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ያሰዩት ምላሽ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
ክልሎች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ታሪካዊ ነውም ብለዋል።
የክልሉ ተመላሽ የሠራዊት አባላትና የጦር መኮንንኖች ሠራዊቱን ተቀላቅለው እየተፋለሙት እንደሚገኙም ገልጸዋል።
አሸባሪው ትህነግ በውጊያው ከሕፃናት እስከ አዛውንት ድረስ እያሰለፈ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን እያስጨረሰ ነው፣ ጦርነት የማያውቁ ሕፃናት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ጉዳት እየደረሰባቸው ነውም ብለዋል፡፡
የትህነግ ዓላማ የአማራን ሕዝብ ለማጥቃትና ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያለመ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ጠላት ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነው ብለዋል። በራያና በጠለምት ግንባሮች የጁንታው ጀሌዎች እንደ ቅጠል እየረገፍ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት እየታገለ የመጣ ጀግና ሕዝብ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ አማራ ማን እንደሆነ ያውቁታል፣ ይህን ሕዝብ ለማንበርከክ የትኩረት አቅጣጫ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነውም ብለዋል።
አሸባሪውን ቡድን የአፋርና የአማራ ሕዝብ እየተፋለመው ነውም ብለዋል። በሕዝቡ፣ በልዩ ኃይሉና በመከላከያ ሠራዊት ትህነግን የመምታት ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ይህ ኃይል እስካልጠፋ አናርፍም ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ። የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፣ ጦርነቱ የአማራን ሕዝብ ሕልውና የምንታደግበት ነውም ብለዋል።
የሕልውና ጦርነቱን በአሸናፊነት ለመጨረስ የአማራ ሕዝብ አስተዋጽኦ የጎላ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ርእሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው በክልሉ ውስጥ የማንኛውም የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሣሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ሁሉ ከነገ ጀምሮ በሁሉም ማዕከል እንዲከት የክተት ጥሪ ተላልፏል።
ሁሉም የክተት ጥሪውን ተቀብሎ ለፀረ ትህነግ ዘመቻ መዘጋጄት አለበት ብለዋል። የክተት ጥሪው አማራንና ኢትዮጵያን የመታደግ ጥሪ ነውም ብለዋል።
ሀገር የማፈረስ ዓላማ ያለውን ኃይል በተባበረ ክንድ መደምስ አለብን ነው ያሉት።
አሁን በገጠምንበት አውደ ውጊያ ከፍተኛ ከሲሳራ እየገጠመው ነው፣ ወደ ትግራይ ተመልሶ መሄድ አይፈልግም፣ ምክንያቱም ለትግራይ እናቶች የሚሰጠው መልስ የለውም፣ ስለዚህ ህልሙን ማጨናገፍ አለብን ብለዋል፣ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነውን ከሀዲ ቡድን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሁሉም መነሳት አለበት ነው ያሉት።
በአሉባልታ ሊያፈርሱን ስለሚፈልጉ ከአሉባልታ መጠበቅ ይገባል፣ በአንድነት ማሸነፍ አለብንም ብለዋል። በሁሉም ግንባር የጠላትን ኃይል ዋጋውን እየሰጠነው ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ሕዝቡ ከጎናችን መሆኑን መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ መረጃ እንደሚያስፈልገው እናውቃለን ነገር ግን ሁሉም የጦርነት መረጃ ስለማይነገር በትዕግሥት መጠበቅ ይገባል፣ አስፈላጊ መረጃ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ይሰጣልም ብለዋል። መረጃ ከትክክለኛው አካል መውሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሁሉም ሕዝብ በትህነግ ፕሮፖጋንዳ ሳይደናገጥ የቡድኑን እኩይ ድርጊት መታገል እንዳለበትም ገልጸዋል።
ሠርጎ ገብነት ላይ ሕዝቡ እንዲጠነቀቅም አሳስበዋል፣ የትግራይ ሕዝብ ወንድማችን ነው፣ ትግሬ የሆነ ሁሉ ጠላታችን አይደለም፣ በትህነግ ፕሮፖጋንዳ ተሳስቶ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ እየተዋጋ ነው፣ አሁንም መላው የትግራይን ሕዝብ አይወክልም ነው የምንለው፣ ነገር ግን የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ወደጦርነት ከማሰለፍ መታቀብ አለባቸው፣ የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ ስህተት እየፈፀመ ነው፣ ወያኔን በቃህ ማለት አለበት፣ በክልላችን የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በሰላም እንዲኖሩ እንፈቅዳለን፣ ለጠላት የሚያብሩ ካሉ ግን ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን ነው ያሉት።
የአማራን መሬት ለወያኔ እሾህ እናደርገዋለን፣ በየትኛውም አቅጣጫ ሊንቀሳቀስ እይችልም፣ ሁሉም በየደረጃው መደራጄት አለበት፣ ወደ ግንባርም መሄድ አለበት ነው ያሉት። ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጀመሩትን አኩሪ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅቱ ለአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ወቅት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ታሪክ የምንሰራበት ነው፣ ባንዳን መቅበር ደግሞ የአማራ ሕዝብ ያውቅበታል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
May be an image of 1 person, sitting and indoor
0
People Reached
0
Engagements
Distribution Score
Boost Post
Like

 

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.