Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ የሚፈለጉ 1 ሺህ 600 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ አልተቻልም- ጠቅላይ አቃቤ ህግ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ ከሚፈለጉ 3 ሺህ ተጠርጣሪዎች 1 ሺህ 600 ገደማ የሚሆኑትን ለህግ ማቅረብ እንዳልተቻለ የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለፀ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው በስብሰባውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ፥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፉት ስድስት ወራት በፍትህ ጉዳዮች ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

የተገልጋይ አመለካከትና አመኔታ ልኬት የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም በተቋሙ ላይ የተገልጋይ አመለካከትና አመኔታ 71 በመቶ እንደሆነም በሪፖርታቸው አቅርበዋል።

እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የወንጀል ህጉን ለማስጠበቅና ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ የወንጀል መከላከል ስራን ውጤታማ ለማድረግ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ነው ያስታወቁት።

የሁሉም የወንጀል አይነቶችን የማጥራት ምጣኔ 100 በመቶ ለማድረግ ታቅዶ፤ የምርመራ ሂደታቸው የተጠናቀቁ 27 ሺህ 959 የክስ መዝገቦች ቀርበው 27 ሺህ 684 መዛግብት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፤ 175 መዛግብት ደግሞ በሂደት ላይ ይገኛሉ፤ በዚህም የማጥራት ምጣኔው 99 ነጥብ 01 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

ውሳኔ ካገኙት ውስጥ 19 ሺህ 238 መዛግብት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፥ 8 ሺህ 446 በተለያዩ ህጋዊ ምክንያቶች የተዘጉ መሆናቸውንም ነው አቶ ብርሃኑ ያብራሩት።

የማስቀጣት ምጣኔን በአማካይ 96 ነጥብ 1 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 94 ነጥብ 02 ተፈፅሟል ያሉት አቶ ብርሃኑ ፥ በዚህም 32 ሺህ 949 መዛግብት በክርክር ሂደት የነበሩ ሲሆን፥ 7 ሺህ 335 መዛግብት ውሳኔ ሲያገኙ፤ ከእነዚህ ውስጥ 6 ሺህ 897 መዛግብት የጥፋተኝነት፣ 438 መዛግብት ደግሞ የነፃ ውሳኔ ያገኙ ናቸው ብለዋል።

ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አፈፃፀም ለማሻሻል ባለፈው በጀት ዓመት የተጀመሩ እና በበጀት ዓመቱ አዲስ የተከፈቱ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የሙስና ወንጀሎች ትኩረት በመስጠት ሲሰራ መቆየቱንም አብራርተዋል።

በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራ እና ለክስ ከሚፈለጉ 3 ሺህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ለህግ ማቅረብ የተቻለው 1 ሺህ 404 የሚሆኑትን ነው ብለዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 1 ሺህ 600 ገደማ የሚሆኑትን ለህግ ማቅረብ አልተቻልም ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ እነዚህም ተጠርጣሪዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 827፣ በደቡብ ክልል 655፣ በኦሮሚያ 50፣ በአማራ 18፣ በትግራይ 4፣ በሶማሌ 33፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ 9 ተጠርጣዎች ክስ ተመስርቶባቸው እንዳልቀረቡ በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል።

ተጠርጣሪዎቹን ለህግ ማቅረብ ያልተቻለው ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ነው ብለዋል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ።

ከሙስና ጋር በተያያዘም ከስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተቀበሏቸው 360 መዛግብት ላይ ውሳኔ ለማሰጠት መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች እየተሟሉ ነው ብለዋል።

በሙስና ከገንዘብ ቅጣት 10 ሚሊየን 476 ሺህ እንዲሁም ክስ ከተመሰረተባቸው ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መደረጉን ገልፀዋል።

ተቋሙ በቀጣይ የተገኙ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና ችግሮን ለመፍታት የቀጣይ 10 ዓመታት እቅድ ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

የተደራጁ ወንጀሎች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሙስና እና ክስ ተመስርቶባቸው በቁጥጥር ስር ያልዋሉት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ተግባራት በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.