Fana: At a Speed of Life!

በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ምርመራ ነፃ መሆናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ምርመራ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን ለተጨማሪ ምርመራ ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩ ተገለፀ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጡት መግለጫ እነዚህ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን የሰውነታቸው የሙቀት መጠን ከፍ በማለቱ በጥርጣሬ በኳረንቲን ተለይተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እስካሁን በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን ያስታወቁት ተቋማቱ ነገር ግን ከቻይና ውሃን (Wuhan) ግዛት ካለው ዩኒቨርሲቲ የመጡ 4 ተማሪዎች መካከል አንዱ የጉንፋን መሰል ምልክቶች የታዩበት በመሆኑ ሌሎቹንም ሶሰት ተማሪዎች አብረው የመጡ በመሆናቸው በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ ብለዋል።

ለአራቱም ተጠርጣሪዎች በሀገር ውስጥ የላቦራቶሪ ናሙና ተሰርቶ ለጉንፋን መሰል በሽታ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ለከፍተኛ ምርመራ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳልም ነው ያሉት።

ከተወሰደው ናሙና በሀገር ውስጥ በተደገላቸው ምርመራ ከአምስት ዓይነት ኮሮና ቫይረሶች ነጻ መሆናቸውን ማወቅ መቻሉን አረጋግጠዋል።

አራተኛው ተጠርጣሪ የጉንፋን መሰል ምልክት ያሳየ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት የሁሉም ተጠርጣሪዎች የጤና ሁኔታ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ከቻይና ጓንዡ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሁለት ቻይናውያን መኖራቸውን የቻይና ኤምባሲ ባደረገው ጥቆማ መሰረት ተጓዦቹ በአውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የምርመራ ቦታ ለሁለት ሰዓታት አስፍላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ቫይረሱ ካለበት አካባቢ ጋር ምንም ግንኙነት የለላቸውና በሙቀት ልየታ መሳሪያውም የተገኘ ምልክት ስለሌለ ወደ አገራቸው በሰላም የተመለሱ መሆናቸውን ገልዋል።

ቦቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ያለውን የምርመራ ስራ በተመለከተ የተጓዦች የጉዞ መረጃና ከማን ጋር እንደተገናኙ የሚያሳይ መረጃ በመሰብሰብ የምርመራ ስራው እየተካሄደ እንደሆነና፥ ለዚህ ስራ በሶስት ፈረቃ ተጨማሪ ባለሙያዎች ተመድበው እየተከታተሉት እንደሚገኙም አስታውቋል።

እየተደረገ ባለው ምርመራ ላይ ጥንቃቄ እና ትኩረት ከማድረግ አንጻር ከአየር መንገድ እና ከተለያዩ ኤምባሲዎች ጋር የመረጃ ልውውጥ እና በጋራ የመስራት ስራው ተጠናክሮ እንደቀጠለና በኢትጵያ በሚገኙ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያዎች የእስክሪኒግ ስራ ለመጀመር ዝግጅቶች ማጠናቀቃቸውን ነው የገለፁት።

በተለይም ከቻይና ለመጡ 280 መንገደኞች በየዕለተቱ ባረፉበት ቦታ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፥ ይሄም ክትትል ለ14 ቀናት የሚቆይ ነው ተብሏል።

በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍልና የሰዉሃይልን ጨምሮ አስፈላጊዉ ግብአት ተዘጋጅቶዋል።

በበሽታው ለተጠረጠሩ መንገደኞች የጊዚያዊ ማቆያ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ የተዘጋጀ ሲሆን፥ የከፋ ሁኔታ ላልታየባቸው 30 ለሚሆኑ በበሽታዉ የሚጠረጠሩ ታካሚዎችን የሚይዝ የለይቶ ማከሚያ የህክምና መእከል በቦሌ ጨፋ ተዘጋጅቶ አስፈላጊዉ የህክምና እና ልዩ ልዩ ግብአቶች እየተሟሉ ይገኛሉም ነው የተባለው።

በዚህ ማእከል በሽታዉ የተረጋገጠባቸዉ፣ የተጠረጠሩ እና ተለይቶ ክትትል ለሚደረግላቸዉ ክፍሎች ተለይተው ተዘጋጅቶዋል።

በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል መዘጋጀቱ ነው የተጠቆመው።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.