Fana: At a Speed of Life!

ኤርትራዊያን ስደተኞች በአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች አሰቃቂ ግፍ እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኤርትራዊያን ስደተኞች በአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች አሰቃቂ ግፍ እየተፈጸመባቸው በመሆኑ ለደህንነታቸው አስተማማኝ ወደ ሆነ አካባቢ እንዲዛወሩ ጠየቁ።

አሸባሪው ህወሃት በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ በኤርትራውያን ላይ የግድያ፣ የዘረፋ፣ የሰው ማገትና የአስገድዶ መድፈር ተግባራትን እንደሚፈጸም ተገልጿል።

በትግራይ ክልል በማይ ዓይኒ እና አዳ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች የሚደርስባቸው ግፍና መከራ ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ መከራና ስቃይ በመውጣት ደህንታቸው ወደሚጠበቅበትና ሰላም ወደ ሚያገኙበት አካባቢ እንዲዛወሩ ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና የአሜሪካ መንግስት ትናንት በተናጠል እንደገለጹት፤ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአሸባሪው ህወሃትን እኩይ ተግባር ባልኮነኑበት በዚህ ገለጻቸው፤ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ዛቻ እንዲሁም ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ ሪፖርቶች እየደረሱን በመሆኑ ጉዳዩ አሳስቦናል ብለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጄሊና ፖርተር ÷ በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን በትግራይ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ  እየደረሱ ያሉትን ዛቻ እና ጥቃቶች የሚገልጹ ተጨባጭ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው ተናግረዋል።

ጥቃቱ በአፋጣኝ እንዲገታም አሜሪካ ማሳሰቧን ነው የገለጹት።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ባወጣው መግለጫ÷አሸባሪው ህወሃት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች በመግባት ቢያንስ ስድስት ስደተኞች እንደተገደሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ማግኘቱን በመጥቀስ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አድርጎ ነበር።

ስደተኞች እንደሚገልጹትም የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች አሰቃቂ ግፍና በደል እየፈጸሙባቸው ነው።

በርካታ ስደተኞች በታጣቂዎች መገደላቸውንና ወጣቶችም ከስደተኞች ጣቢያ ታፍነው ወደ በረሃ መወሰዳቸውን ነው ያመለከቱት።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚገልጸው ÷በትግራይ ያሉ የኤርትራ ስደተኞች ሰቆቃ እንደቀጠለ ሲሆን፤ በየቀኑ በአሰቃቂ ታሪኮች የተሞሉ አሳማኝ ማስረጃዎችን ይቀበላል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ቀደም ባሉት ጊዜያት አሸባሪው ህወሃት ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ሕግ በመጣስ የአሸባሪው የህወሃት ታጣቂዎች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከባድ መሣሪያዎች መትከላቸውን፤ ቀጣይነት ያለው የታጣቂ እንቅስቃሴ እና አልፎ አልፎም ተኩስ እንደሚሰማ አስታውቆ ነበር።

ኤጀንሲው ስደተኞች ከሚገኙበት አደገኛ ሁኔታ እና የእገታ አዝማሚያ ለመታደግ የሚያደርገውን ጥረትም እንዲደግፉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጥሪ ማቅረቡም ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት ግን አሸባሪው ህወሃት ድርጊቱን እንዳላቆመና በስደተኞቹ ላይ የበለጠ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በተለያየ መንገድ እየገለጸ ይገኛል።

ኤርትራውያን ስደተኞች እንደገለጹት፤ ታፍነው የተወሰዱ በርካታ ወጣቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሆኑ አይታወቅም።

ታጣቂዎቹ በስደተኞች ላይ እየፈጸሙ ያሉት አሰቃቂ ተግባር በሁሉም ስደተኛ ጣቢያዎች ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በትግራይ ክልል ከሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎች በአፋጣኝ አውጥቶ ሰላምና ደህንነታቸው ወደሚረጋገጥበት አካባቢ እንዲወስዳቸው ነው የጠየቁት፡፡

“እኛ የማንም ፖለቲከኛ ተላላኪዎች አይደለንም” ያሉት ስደተኞቹ÷ በተለይ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ካሉበት አሰቃቂ ቦታ ደህንነቱ ወደተረጋገጠና አስተማማኝ ወደ ሆነ ጣቢያ እንዲወስዷቸው ጠይቀዋል፡፡

ህወሓት በስደተኞች ላይ እየፈጸመ የሚገኘውን ግፍና በደል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ማውገዝ እንዳለበትም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በሰጡት አስተያየት ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል የገቡትን ስደተኞች ለማቋቋም እየተሰራ ነው፡፡

ሌሎች አጋር አካላት ግን በሚፈለገው መጠን ስራቸውን እየሰሩ አለመሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ በገቡት ውል ስምምነት መሰረት የሚያሥፈልገውን ሁሉ እንዲያቀርቡም ማሳሰባቸው ይታወሳል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.