Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር ቴድሮስ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በቤጂንግ ተገናኝተው ተወያዩ።
 
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ለመምከር ቻይና ቤጂንግ ይገኛሉ።
 
በቤጂንግ ቆይታቸውም ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተወያዩ ሲሆን፥ በውይይታቸውም በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና ሀገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል እያደረገች ባለው ጥረት ዙሪያ መክረዋል።
 
በተጨማሪም ዶክተር ቴድሮስ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ዋንግ ዪ ጋርም በቤጂንግ ተገናኝተው መክረዋል።
 
በዚሁ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፥ ቻይና በሽታውን ለመከላከል ያላት አቅም እና እየወሰደች ያለው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን አስታውቅዋል።
 
የቻይና መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ፥ የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና እንዲህ አይነት ወረርሽኞችን ለመከላከል ያላት አቅም ላይ ሙሉ እምነት እንዳለውም ገልፀዋል።
 
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትም የዓለም ጤና ድርጅት ከቻይና ጋር በትብብር እንደሚሰራ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።
 
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው፥ ቻይና የቫይረሱን ስርጭት በቅርብ ቀናት ውስጥ ለመግታት ሙሉ አቅም እና በራስ መተማመን እንዳላት አስታውቀዋል።
 
በተያያዘ ዜና በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሟቾቹ ቁጥር 106 መድረሱንና ከ4 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መጠቃታቸውን በዛሬው እለት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
 
የኮሮና ቫይረስ በሽታ ከቻይና በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ በ16 ሀገራት መከሰቱ የተጠቆመ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በታይላንድ በ8 ሰዎች ላይ፣ በጃፓን በ6 ሰዎች ላይ በአሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ታይዋን እና ሲንጋፖር በአምስት አምስት ሰዎች ላይ፣ በማሌዢያ እና ደቡብ ኮሪያ አራት አራት ሰዎች ላይ፣ እንዲሁም በፈረንሳይ፣ በቬትናም፣ በኔፓል፣ በካናዳ፣ በካምቦዲያ፣ በስሪላንካ እና በጀርመን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸው ተነግሯል።
 
 
ምንጭ፦ ዠንዋ እና ቢቢሲ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.