የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕልውና ዘመቻው ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል አስረከበ

By Meseret Awoke

July 29, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕልውና ዘመቻው የሚውል ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል አስረክቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕልውና ዘመቻው የሚያደርገው ድጋፍ በአራት አቅጣጫ የተመራ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአፋር ክልል እና በአማራ ክልል በጎንደር እና በኮምቦልቻ በኩል እንዲደርስ እየተደረገ ነውም ተብሏል፡፡

በጎንደር በኩል ላለው የሕልውና ዘመቻ በግንባር የተደረገውን የከተማ አስተዳደሩን ድጋፍ ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኅላፊ አቶ ዘላለም ሙላት ናቸው፡፡

በዓይነት የተደረገው ድጋፍ ከከተማ አስተዳደሩ ባለሃብቶች እና ነዋሪዎች የተሰበሰበ መሆኑንም አቶ ዘላለም የገለጹ ሲሆን፥ 139 ሰንጋ፣ 1 ሺህ 809 በግና ፍየል፣ በሁለት መኪና የተጫነ ብስኩት፣ 121 ኩንታል ጤፍ እና ምግብ ነክ ቁሳቁስ ናቸው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪዎቿም ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማስታወቃቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኅላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ፥ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መዲናነቷን በተግባር ስታረጋግጥ ይህ ድጋፍ የመጀመሪያዋ አለመሆኗን ገልጸዋል፡፡

የአማራ እና የአፋር ክልሎች ፊት ለፊት የተገኙ እና የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ቢያስመስላቸውም አሸባሪው ቡድን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕልውና ስጋት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ እና ላሳየው አጋርነት የአማራ ክልል መንግሥት እውቅና ይሰጣልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልዑክ ድጋፉ በተጓጓዘባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ላሳየው አብሮነት እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ላደረገላቸው አቀባበል ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!