የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የአለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ገለጸ።
ለአንድ ሳምንት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተለያዩ የስራ ክፍሎችን ሲገመግም የቆየው የአለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የልኡካን ቡድን በዛሬው እለት የቅድመ ምዘና (ኦዲት) ሪፖርቱን አቅርቧል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በፈረንጆቹ 2019 እጅግ ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ነው ያስታወቀው።
የልኡካን ቡድኑ መሪ ኡስማን ኬሞ ማጃንግ፥ በፈረንጆቹ 2019 በጀት አመት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቅድመ ምርመራ የስራ አፈፃፀም በፊት ከነበረበት 73 ነጥብ 2 ደረጃ በበጀት ዓመቱ ወደ 91 ነጥብ 78 ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ ኃላፊዎች፣ የግል ኦፕሬተሮች እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የስራ ክፍል ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።