የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ በዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት ቀረበ

By Tibebu Kebede

July 29, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር በጣሊያን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት ቀረበ፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዘጋጅነት በጣሊያን ሮም ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የስነ ምግብ ስርዓት ኮንፈረንስ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተሳትፈዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ የስነ ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የመንግስት አጀንዳ ሆኖ እየተሰራ እንደሚገኝ በዚህ ወቅት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የስነ ምግብ ዘርፍ አማካሪ ሜቲ ታምራት በከተማው እየተከናወነ ያለውን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተሞክሮን ከአዲስ አበባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው በጀት ዓመት ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በመመደብ በከተማዋ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።

በዚህም ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የተማሪዎችን ወጤት በማሳደግ፣ የመድገምና የማቋረጥ ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

በምገባ ፕሮግራሙ ምግብ በማብሰል ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ ተደርጓል ማለታቸውን የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያመላክታል።

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በአምስት ክፍለ ከተሞች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በመለየት የምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ የመመገቢያ ማዕከላትን በማቋቋም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!