Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ጋርኑ ጋር ተወያዩ፡፡

ውይይታቸውም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በተጨማሪም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች መክረዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅት የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዱ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትግራይ ስላለው ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ሁኔታ ሲወያዩ እንዳሉት፥ ሃገራቸው ወደ ክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍሰት ፍጥነት እንዲሻሻል ትጠብቃለች ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፥ የፌዴራል መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ለማወጅ መወሰኑ በአካባቢው ያሉ ሰብዓዊ ሥጋቶችን ለመቅረፍ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል ፡፡

ህወሃት በተኩስ አቁም ስምምነቱ የሰላም ዕድሉን በማባከኑ እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት በአፋር እና በአማራ ክልሎች አዲስ ጥቃቶችን መጀመሩን ተናግረዋል ፡፡

አክለውም መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ፣ ሰላም እና መረጋጋት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባለመስጠቱ ስጋቱን ገልፀዋል ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ካናዳን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ የሰብአዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲያከብር ፣ የሰብአዊ ድጋፍ ማደናቀፍ መቀጠሉን እና የጥፋት ድርጊቶቹን እንዲያቆም ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

ቡድኑ አዲስ በከፈተው ጥቃት ከ200ሺህ በላይ ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል ፡፡

በመጪው መስከረም ሥራውን የሚጀምረው አዲሱ መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሁሉን ያካተተ ውይይቶችን ለማካሄድ ዕቅድ መያዙን ገልጸው፥ ኃላፊነት የጎደለው ይህ ቡድን ህጻናትን ወደግንባር በማሰላፍ ግጭቱን ለማባባስ የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያቆም ሊነገረው ይገባል ብለዋል ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.