Fana: At a Speed of Life!

ለቀረበው ሀገራዊ ጥሪ የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት ለህግ ማስከበር ዘመቻው ወደ ግንባር አመሩ

 

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥሪውን በመቀበል ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የጸጥታ አካላት በፌዴራል ፖሊስ አስተባባሪነት ለህግ ማስከበር ዘመቻው ወደ ግንባርና ወደ ተመደቡባቸው አምርተዋል፡፡

ሀገራዊ ጥሪውን በመቀበል የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስተባባሪነት ለህግ ማስከበር ዘመቻው ወደ ግንባርና ወደ ተመደቡባቸው ሌሎች የስምሪት ቦታዎች ማምራታቸውን ነው ፌደራል ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

መንግስት የሰጠውን የእፎይታ ጊዜና የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል የአሸባሪ ጁንታ ህወሃት ቡድን ርዝራዦች በህዝብና በሰራዊቱ ላይ እየፈፀሙ ያሉትን የሽብር ተግባር በመመከት በቡድኑም ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ከየአቅጣጫው ለተንቀሳቀሰው የፖሊስ ልዩ ኃይል በፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎ የስራ መመሪያም ተሰጥቷል፡፡

ከዚህ ቀደም አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን ለፖሊስ ልዩ ሃይል አደረጃጀት ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ እኩይ አጀንዳዎችን ቀርፆ በመስጠት የፖለቲካ መጠቀሚያ አድርጓቸው እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ቀደም ሲል በአሸባሪው ተከፋፍሎ የነበረውን የፖሊስ ልዩ ኃይል ወደ አንድነት በማምጣትና የቀደመውን አፍራሽ አስተሳሰብና አመለካከት በመስበር ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በአንድ ማሰለፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡

የህዝብ የጋራ ጠላት የሆነውና ሀገርን የማፍረስና የመበታተን ዓላማ ያነገበው፣ አሸባሪ የህወሃት ጁንታ ቡድንን ለመደምሰስ የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላቱ ከሀገር መከላከያና ከፌዴራል ፖሊስ ጎን በመሰለፍ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለህግ ማስከበር ዘመቻው ሀገራዊ ተልዕኮና ግዳጅን ተቀብለው ተሰማርተዋል፡፡

የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላቱ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበርና በዜጎች ላይ የሚቃጣ ማንኛቸውንም የሽብር ተግባራት ለመመከት በሚደረገው ዘመቻ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛና ዝግጁ መሆናቸውን በመግለፅ የሚሰጣቸውን የትኛውንም አይነት ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት፣ በሰብዓዊነትና በጀግንነት ለመወጣት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.