በንግድ ስርዓት ውስጥ የደላሎችን አሉታዊ አካሄድ ማስቆም ካልተቻለ የዋጋ ግሽበት ሊያሻቅብ ይችላል-ምሁራን
አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የንግድ ስርዓት ውስጥ የደላሎችን አሉታዊ አካሄድ ማስቆም ካልተቻለ የዋጋ ግሽበቱ ከዚህም በላይ እያሻቀበ ሊሄድ እንደሚችል የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧ የሚነገርላት ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ፈተና ሆኖባታል ተብሏል።
መንግስት ደላሎች በሚፈፅሙት የኢኮኖሚ አሻጥር በየጊዜው የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት መቆጣጠር እንደሚገባው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ ፡፡
ለዋጋ ግሽበቱ የውጪ ንግድ እና ኢንቨስትመንት መዳከም እንዲሁም የመንግስት የቁጥጥር ስርዓት መላላት ድርሻ አላቸውም ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ የገቢ እና ወጪ ንግድ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የስራ አጥነት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮች ልዩነቱ እየሰፋ መሄዱም ይነገራል ።
የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ፥ ለሚስተዋሉት ችግሮች የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም ኢኮኖሚው በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚታየው ችግር ነፀብራቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ አቶ ሀይለመለኮት አስፋው በበኩላቸው፥ በአሁኑ ወቅት ሁላችንም የፖለቲካ ተንታኝ እንጂ ስራ ላይ ውጤታማ ስንሆን አንታይም ብለዋል፡፡
ይህ ደግሞ የፍላጎት እና አቅርቦት ልዩነቱ የተራራቀ እንዲሆን ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በርካታ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል ንብረት እንዲወድም እና የስራ እጦች ችግሮችም እንዲፈጠሩ ማድረጉም ነው የተገለጸው፡፡
ይህንን አለመረጋጋትን እንደ መልካም እድል የሚጠቀሙ ደላሎች ግን ከዚህ ክስተት ለማትረፍ መሞከራቸውን ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ምርቶችን በብቸኝነት የሚያመጡ ተቋማት ዋጋን እንደፈለጉ የመተመን ችግር እንደሚታይባቸው ይነገራል።
ምርቶችን በመደበቅ እጥረት ፈጥሮ ዋጋን ለማናር የሚፈፀሙ ድብቅ ተግባራት እንደሚፈፀሙም የንግዱ ማህበረሰብ ጭምር የሚታዘቧቸው ጉዳዮች ናቸው።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማከም በቅድሚያ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የፐብሊክ ፖሊሲ የህግ እና ታክስ አማካሪው ፕሮፌሰር መንግስቱ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን ህገ ወጥ አካሄድ የሚመቻቸው ደላሎች የመንግስት ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ መስጠት ላይ አተኩሮ ቁጥጥሩ ማላላቱን ተጠቅመው በምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዲከሰት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከፋና ብሮድካስትጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ልዩ ትስስር በመፍጠር የንግድ ስርዓቱን እያወኩ ያሉ ባለሃብቶችንም መቆጣጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተለይ በመሰረታዊ ግብዓቶች ላይ በየጊዜው ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ የሚያደርጉ እና በህዝብ ላይ የሚነግዱ ህገወጥ ባለሃብቶችን በመለየት እርምጃ መውሰድ አለበትም ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በነፃ ኢኮኖሚ ስም ያልተገባ ድርጊት እየፈፀሙ ያሉ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የፖለቲካዊ ችግር ዋነኛው መንስኤ ከድህነት እና ስራ አጥነት ጋር የተገናኘ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ፍስሃጺዮን፥ ለኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ መፍትሄ መስጠት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ ውስብስብ እንደመሆናቸው መጠን መፍትሄያቸውም አንድ አይደለም ያሉት ምሁራኑ ፥ ይህንን ችግር በቀላሉ ለመፍታትም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅበዋል።
በሌላ በኩል የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በማስፈን የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ማነቃቃት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላክቷል።
በፋሲካው ታደሰ