Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ፌሮ ብረት ክምችት ለማስለቀቅ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረብና ጉቦ በመስጠት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ፌሮ ብረት ክምችት ለማስለቀቅ የሞከሩ ተጠርጣሪዎችን መያዙን የፌዴራል ፖሊስ ገለፀ።
ባለፈው ሳምንት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቡልቡላ አካባቢ በአንድ መጋዝን ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለና በምርመራ ሂደት ላይ ያለ በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመት የፌሮ ብረት “ህጋዊነቱ ስለተረጋገጠ በቦታው የሚገኘው የፖሊስ ጥበቃ ተነስቶላቸው ወደ ፈለጉበት ማንቀሳቀስ እንዲችሉ ፈቅደናል” የሚል ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የተፃፈ በማስመሰል ሀሰተኛ ደብዳቤ አዘጋጅተው በመያዝና ጉቦ ለመስጠት የሚውል ገንዘብ ባንክ አስገብተውና በቼክ አዘጋጅተው ብረቱን በአምስት ተሽከርካሪ ጭነው ሊወጡ ሲሉ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስና በፋይናንስ ኢንተለጀንስ ጠንካራ ክትትል ሊያዙ ችለዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉትም እምሩ ከበደ ሀጎስ ወይም ሀብቶም፣ ደመላሽ አድማስ ታምርና ወይዘሮ ዳግማዊት መስፍን የተባሉ ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት የተያዘው ብረት ባለቤት ነኝ ከሚል፣ ተክላይ ከሚባልና አሜሪካን ሀገር ነዋሪ ነው ተብሎ ከሚነገረው ግለሰብ ጋር ሶስቱ ተጠርጣሪዎች የጥቅም ትስስር በመፍጠር በኤግዚቢትነት ተይዞ በምርመራ ሂደት ላይ ያለውን የፌሮ ብረት በጥበቃ ላይ ላሉት የፖሊስ አባላትና አመራሮች 500 ሺህ ብር ጉቦ ለመስጠት በአቢሲኒያ ባንክ አዲስ አካውንት ከፈተው ያስገቡ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይም ለሌሎች የፀጥታ አካላት 400 ሺህ ብር በባንክ እና የ25 ሚሊየን ብር ቼክ አዘጋጅተው ብረቱ እንደሚለቀቅ ከተስማሙ በኋላ የፖሊስና የፀጥታ አካላቱ ጉዳዩን ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ለበላይ ሃላፊ በማሳወቅ ሂደቱ እንዲቀጥል በመደረጉ ብረቱን በአራት ሲኖትራክ እና በአንድ ክሬን ለመጫን ተስማምተው በሁለት ሲኖትራክ እንደተጫነ ባንክ የገባው ብር እና ቼኩ፣ እንዲሁም የተፃፈው ሀሰተኛ ደብዳቤ እና ሶስቱ ተጣርጣሪዎች በተጨማሪም
ኮድ 3- 63911 ኢት ሲኖትራክ፣ኮድ 3- 80559 ኢት ሲኖትራክ፣ኮድ 3-67732 ኢት ሲኖትራክ፣ኮድ 3-67617 ኢት ሲኖትራክ እና ኮድ 3-53243 ኢት ክሬን ክራፍት ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከነአሽከርካሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
ብረቱ ባለፈው ሳምንት በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በምርመራ ሂደት ላይ ያለ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ ለፀጥታ አካላት በርካታ ገንዘብ ሰጥተው በማማለል ለህገ- ወጥ ድርጊት ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደረጉትን ጥረት በማክሸፍና ለህግና ለመንግስት ፍፁም ታማኝ በመሆን ወንጀሉ ለህግ እንዲቀርብ በማድረግ የጁንታውን እኩይ ሴራ ማክሸፍ መቻላቸው ታውቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስም የፀጥታ ሀይሎቹ ለሙያ ስነ-ምግባር ተገዥ በመሆንና ለህዝብና ለመንግስት የገቡትን ቃል-ኪዳን በመጠበቅና በማክበር ለፈፀሙት ሙያዊ ተግባር ከፍተኛ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ህብረተሰቡ አሁንም በዚህ አይነት የወንጀል ተግባር ላይ ለመሳተፍ የሚጥሩ ጁንታውና ከጁንታው ጋር ግንኙነት ፈጥረው ሀገራችን ላይ የሚያሴሩ ባንዳ ግለሰቦችን እየጠቆመ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.