Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ ከ16 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የገቢና የወጪ እቃዎችን አጓጓዘ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የማሪያታይም ጉዳይ ባለስልጣን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ16 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የገቢና የወጪ እቃዎችን ማጓጓዙን አስታወቀ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከወደብ የገቢና የወጪ እቃዎችን የማንሳት ጥረት አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ተናግረዋል።

“ዘመናዊ የሎጂስቲክ አገልግሎት አሰጣጥ ማቀላጠፍ፣ አማራጭ ወደቦችን መጠቀምና የባቡር የጭነት አቅም መሻሻል ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ ሚና ነበረው” ብለዋል።

በዚህም ሀገሪቱ ለትራንስፖርት አገልግሎት ልታወጣ የነበረውን 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መቆጠብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በአዲሱ የበጀት ዓመት የሎጂስቲክ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ 2 ሺህ 400 አዳዲስ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ በግዥ ሂደት ላይ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጨማሪም አማራጭ ወደቦች የመጠቀምና የሎጂስቲክ አገልግሎቱን የማዘመን ስራ ቀዳሚ ትኩረት ማግኘታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በባለስልጣኑ የጭነት የሎጂስቲክ ስርዓት የእቅድ ዝግጅትና ሪፖርት ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጫልችሳ በበኩላቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ16 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የገቢና የወጪ እቃዎችን ማጓጓዝ ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.