Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ተቋማት ሃገርን ከውድቀት የሚታደግ ትውልድ መፍጠር ይገባቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃገር ግንባታ የሚጀመርባቸው የትምህርት ተቋማት ሃገርን ከውድቀት የሚታደግ ሚና መጫወት የሚችል ትውልድ መፍጠር ይገባቸዋል ተባለ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከትምህርትና ከትምህርት አጋር አካላት ጋር፥ የትምህርት ተቋማት ለሃገር ግንባታ ማበርከት በሚገባቸው ሚና ዙሪያ ምክክር እያደረገ ነው።

በመድረኩ የትምህርት ተቋማት፣ ስርአተ ትምህርቱ፣ መምህራንናን ተማሪዎች የሃገራቸውን ባህል ጠንቅቀው የተረዱና ያወቁትን በአግባቡ ለተተኪው ትውልድ የሚያስተላልፉ መሆን ይገባቸዋል ነው የተባለው።

በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ ምሁራን የመነሻ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

ምሁራኑ የትምህርት ተቋማትና መምህራን ቤተሰብ ወልዶ የሚሰጣቸውን ትውልድ በማቃናት ለሃገር ልማት ፋይዳ እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ዓለም በቴክኖሎጂ ፈጠራ ታግዞ ግዑዝ ነገሮች እርስ በርስ እንዲግባቡ ባደረገበት ዘመን፥ በኢትዮጵያ ያለው ደካማ የትምህርት መሰረት አሁን አሁን ሰው ከሰው እንኳን እንዳይግባባ እያደረገው ነው ብለዋል።

የመረጃና የተግባቦት ምንጭ የሆነው ትምህርት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሃገራት የማንነትን ውስጣዊ ስሜት በማሳደግ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተና ስልጡን ማህበረሰብ የመፍጠር ተልዕኮ ሊኖረው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሃገሪቱ የትምህርት ስርዓትም በአዕምሯዊ ዕድገት ላይ ማተኮር ይገባዋል ነው ያሉት ምሁራኑ።

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.