Fana: At a Speed of Life!

ከተቋቋሙለት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የውጭ ድርጅቶች ታገዱ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 28፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ከተቋቋሙለት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶስት የውጭ ድርጅቶች ለሶስት ወራት መታገዳቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

አንደኛ MSF HOLLAND ሁለተኛ NORWEGIAN REFUGEE COUNCIL እና ሶስተኛ AL MAKTOUME FOUNDETION የተባሉ የውጭ ድርጅቶች ናቸው የታገዱት፡፡

ድርጅቶቹ የኢትዬጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ በሰጣቸው ፍቃድ በህጋዊነት በተለያዩ የሰብዓዊ ስራዎች ተሰማርተው እየሰሩ የቆዩ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የድርጅቶቹን እንቅስቃሴ በተመለከተ ፍቃድ ሰጪው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በሚያደርገው ክትትል መሰረት ድርጅቶቹ ከተቋቋሙለት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል፡፡

አንደኛ÷ MSF HOLLAND እና NORWEGIAN REFUGEE COUNCIL የተባሉ ድርጅቶች የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች ዘዴዎች ሲያሰራጩ በመገኘታቸው፣

ሁለተኛ÷ ሶስቱም ድርጅቶች ስልጣን በተሰጠው አካል የስራ ፍቃድ ያልተሰጣቸውን የውጭ ሃገር ዜጎች ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ከስድስት ወር በላይ ቀጥረው ሲያሰሩ በመገኘታቸው፤

– ሶስተኛ- MSF HOLLAND ድርጅት ስልጣን በተሰጠው አካል ፍቃድ ያልተሰጣቸው የሳተላይት የሬድዬ መገናኛ መሳሪያወችን ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባ የድርጅቱ ሰራተኞች አፍራሽ ለሆኑ አላማ ሲጠቀሙበት እና ይዘው ሲንቀሳቀሱ በጸጥታ አካላት ቀጥጥር ስር በመዋላቸው፣

– አራተኛ- AL MAKTOUME FOUNDETION ድርጅት የትምህርት ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን ባለማክበር ፣ የበጀት አጠቃቀም ግልጽነት የጎደለውና በትምህርት ቤቱ ስም የሚመጣን በጀት ከአላማው ውጭ እየተጠቀመ በመሆኑ እንዲሁም በሰራተኞች አስተዳደር ችግር የታየበት በመሆኑ ምክንያት፤

ድርጅቶቹ ከተቋቋሙት አላማ ውጭና የሃገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ከድርጅቶቹ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ቢደረግም ሊያስተካክሉ አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡

አጠቃላይ ምርመራ ተደርጎ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 77(4) መሰረት አጠቃላይ የድርጅቶቹ እንቅስቃሴ ለሶስት ወራት የታገዱ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ማሳወቁን ከወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.