Fana: At a Speed of Life!

በአባይ ተፋሰስ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሚና ላይ ያተኮረ ሃገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ፣ ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት” በሚል በተፋሰሱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሚና ላይ ያተኮረ ሃገር አቀፍ የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

መድረኩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ባዘጋጁት የምክክር መድረክ በተፋሰሱ የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች የአባይ ተፋሰስን ለማልማት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡና የጋራ መግባባት ላይ የሚደርሱበት ነው ተብሏል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ÷ ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የምታስመዘግበው ድል ከአድዋ ጋር ምሳሌ ይሆናል ብለዋል።

በአድዋ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በቅኝ ገዢዎች ላለመያዝና ነጻነታቸውን ለማስጠበቅ እንደታገሉት የአሁኑ ትውልድም ራሱን ከድህነት ነጻ ለማውጣት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጎን ለጎን ለሚያስፈልጉ ቴክኒካል ጉዳዮች በተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከግድብ በላይ ለኢትዮጵያውያን ህልውና መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዛሬም ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷ በ2013 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 49 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የአገልግሎት ዘመን እንዲረዝም ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለል መቀነስ እንደሚገባ ጠቅሰው÷ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ላይ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በተፋሰሱ ዙሪያ የሚሰሩት ስራ ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሃይማኖት እያሱ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.