ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዩ ኤስ ኤድ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት የሚውል 720 ሚሊየን ዶላር ይፋ አደረገ

By Alemayehu Geremew

August 05, 2021

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩ ኤስ ኤድ የተሰኘው የአሜሪካ ዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅት ለኮቪድ 19 ምላሽ እና ማገገሚያ የሚውል 720 ሚሊየን ዶላር ማፅደቁ ተሰማ፡፡

የአሜሪካ ዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓወር እንደገለፁት በጀቱ የኮቪድ 19 ስርጭትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመግታት ያለመ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም በጀቱ በተለያዩ ሀገራት በቫይረሱ ሳቢያ የተከሰተውን የኢኮኖሚ ችግር ለማነቃቀት እንደሚያስችል ነው የገለጹት፡፡

አሁን ላይ ክትባት ባልተዳረሰባቸው ሀገራት በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እና ወረርሽኙን ለመግታት አስፈላጊው ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከእርዳታው 445 ሚሊየን ዶላር ያህሉ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እንደሚከፋፈል በዘገባው ተመላክቷል፡፡ ከተጠቀሰው መጠን 320 ሚሊየን ዶላሩ የሚውለው በአካባቢው ለተመረጡ 20 ሀገራት ለሚያስፈልግ አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሆነም ነው የታወቀው፡፡

በአሜሪካ 160 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ክትባቱን ሙሉ በሙሉ እንደወሰዱ የተጠቆመ ሲሆን ÷ ከዴልታ ኮቪድ 19 ቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ግን ሀገሪቷ ስጋት ላይ መውደቋ ነው የተገለፀው፡፡