Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪውን ትህነግ አስወግዶ ሰላምን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ትግል ማጠናከር እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪውን የትህነግ ቡድን አስወግዶ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመርነውን ትግል ማጠናከር እንደሚገባ የሲደማ ክልል ጥሪ አቀረበ፡፡

የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ ዛሬ በተጀመረው በምክር ቤቱ 1ኛ የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ሃገር ለማፍረስ እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።

ትህነግ ሃገር የመምራት እድል ባገኘባቸው ባለፉት 27 ዓመታት በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች በተደራጀ መልኩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመቆጣጠርና በመዝረፍ አንዱ ተጠቃሚ ሌላው የበይ ተመልካች በማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለውን ግፍ ፈጽሞብናል ብለዋል።

ጥያቄ የሚያነሱት ዜጎችን በማፈንና በመግደል የተካነው ቡድኑ በጸረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የዓለም አቀፍ ህጎችና ራሱ የፈረማቸው የሰብአዊ መብቶች እየጣሰ ለከፋ ችግር መዳረጉን አውስተዋል።

በህዝብ ግፊት ቦታውን ከለቀቀ በኋላ ‘‘እኔ ያልመራሁት ሃገር ይፍረስ’’ በሚል ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የሃገርን ህልውና የሚፈታተኑ ድርጊቶች ላይ ተጠምዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይባስ ብሎ የሃገር መከላከያ ሠራዊትን በማጥቃት ሃገረ መንግስት ለመቆጣጠር የነበረ ህልም በህግ ማስከበር እርምጃ በመክሸፉ ወደ ሽብር ድርጊት መግባቱን ነው ያመላከቱት።

የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ አድርጎ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በማንገብ በህዝባችን ላይ ጦርነት ማወጁንም ተናግረዋል።

ጦርነቱን መክተን አሸባሪውን ቡድን በማስወገድ የብልጽግና ጉዞችንን ለማረጋገጥ መላው ኢትዮጵውያን እንደቀድሞ አባቶች አንድነታችንን ማጠናከርና መፋለም ይገባል ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው።

በሽብር ተግባር ላይየተሰማራው የትህነግ ርዝራዥ ቡድን ተወግዶ የሀገሪቱ ሰላምና ልማት እስኪረጋገጥ ድረስ በአንድነት የጀመርነውን ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷ አሸባሪው ቡድን በህዝብ መካከል አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዲከሰቱ በማድረግ አንድነትን ለመሸርሸር መሞከሩን ተናግረዋል።

በተለይ የውስጥ ጀሌዎቹን ተጠቅሞ ሲዳማን ከአጎራባች የኦሮሚያና ሌሎች ደቡብ ህዝቦች ጋር ለማጋጨት ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲሰራ እንደነበርም አስታውሰዋል።

እነዚህን የጥፋት ሴራዎች በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ በማክሸፍ ክልሉና አጎራባች አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሰላም ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ከትናንት ስህተቱ የማይማረው ይህ ቡድን አሁን ላይ በሃገር ላይ ያወጀውን ጦርነት ለመመከት ክልሉ በሰው ሃይል፣ስንቅና ሞራል ያለውን ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱ ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የአስፈጻሚ ተቋማት ሪፖርት ላይ እየተወያየ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.