Fana: At a Speed of Life!

የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የቁጥጥር ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ጥር 20፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

በዚህም የተሽከርካሪ የደህንነት ቀበቶ አጠቃቀም፣ የፍጥነት ወሰን፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ምርመራ፣ ህጋዊ የማሽከርከር ፈቃድ ቁጥጥር፣ ከመናኸሪያ ውጭ የሚደረጉና የሌሊት ሕገወጥ ጉዞዎች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡

ቁጥጥሩ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ድንገተኛ የቴክኒክ ምርመራ ማድረግ፣ መንገድ ደህንነት ያላገናዘቡ መንገዶችንና አደጋ የሚበዛባቸውን መንገዶች የመለየት እና ማስተካከያዎች እንዲወሰዱ የቁጥጥርና የማስተማር ስራዎችን ለማከናወን ያስችላል ተብሏል፡፡

የትራፊክ አደጋ የሚያደርሰውን የህይወት እና አካላዊ ጉዳት፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ቀውሶችን መቀነስም የቁጥጥሩ አላማ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዙሪያ ለአሽከርካሪዎች ግንዛቤን ማስጨበጥ፣ የመንገድ ትራፊክ ህጎችን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻልና ደህንነታቸው የተጠበቁ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.