Fana: At a Speed of Life!

እኛ በህይወት እያለን ኢትዮጵያ አትበተንም-የቀድሞ የሠራዊት አባላት

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) እኛ በህይወት እያለን ኢትዮጵያ አትበተንም ሲሉ በደሴ ከተማ የሚገኙ የቀድሞ እና ምልስ የሰራዊት አባላት ተናገሩ።
 
የቀድሞ እና ምልስ የሰራዊት አባላቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ቀድሞም የቆሰልነው፣ የደማነው እና የሞትነው ለኢትዮጵያ አንድነት ነው፤ ዛሬ በህይወት እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም ፡፡
 
ስለሆነም የሀገር ውስጥ ባንዳወችና የኢትዮጵያ ልዕልናን የማይፈልጉ የውጭ ሀገራትን ሴራ ለመበጣጠስ ከመከላከያ ጋር እንሰለፋለን ነው ያሉት።
 
ከከፋተኛ መኮንን እስከ እግረኛ መሠለፍ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹት የቀድሞ የሠራዊት አባቱ ÷ ከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ አመራር ጋር በመነጋገር አደረጃጀት እንዲፈጥርላቸው ጠይቀዋል።
 
ህወሓት በመከላከያ ሠራዊት የጡረታ ጊዜያቸው ሳይደርስና በሴራ በተቀናሽነት ያሰናበታቸው ምልስ የሠራዊት አባላትም መኖራቸውን ገልጸው÷ ለዚህ ሀገር አጥፊ ቡድን ግብዓተ መሬት እኛ ከፊት እንሰለፋለን ብለዋል።
 
የህወሓትን ሴራ ከኛ በላይ የሚረዳው የለም ፤ ሀገር አፍራሽነቱ ከምስረታው ጀምሮ ያለ ነው፤ ይህን እኩይ ቡድንና ሀሣብ እስኪጠፋ ለሀገራችን ዘብ እንቆማለንም ነው ያሉት፡፡
 
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከቀድሞ ሠራዊት አባላት፣ የኢህዴን ታጋዮች እና ምልስ የሠራዊት አባላት ጋር በህልወና ዘመቻው ዙሪያ እየተወያየ ነው፡፡
 
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል÷በመንግስታዊ ተቋማት በርካታ የአሰራር ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ትናንት ከባድ የመልካም አስተዳደር ችግር አሳልፈን ይሆናል፤ ይህ ግን የህልወና ዘመቻውን አያስተጎጉልም ነው ያሉት ።
 
አባላቱ በየዘርፋ ተለይተው ከአካባቢ ጥበቃ እስከ ግንባር አደረጃጀት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግም አቶ አበበ አስረድተዋል።
 
በአለባቸው አባተ
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.