Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን ዘመቻ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኃላፊው በመግለጫቸው እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም በመጣስ ወረራ ፈጽሟል፡፡
አሸባሪው ቡድን ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያን ሰላም ከማይፈልጉ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገር ለማፍረስ በግልጽ ወረራ መፈጸሙን ነው ዶክተር ሰማ ያነሱት፡፡
በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ እንደሚያወራርድ በመዛት የቆየ አማራን የማጥፋት ህልሙን በገሃድ ለመፈጸም እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ህልሙን ለማሳካትም አርሶ አደሮችን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ጭምር እያስገደደ ወደ ጦርነት እየማገደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት የክልሉ የጸጥታ ሃይል ከፌዴራል እና ከሌሎች ክልሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት በሚያካሂዱት ጦርነት በርካታ የጠላት ሃይል መደምሰሱን ጠቅሰዋል፡፡
አሁንም ይህንን ወራሪ እና አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያነሱት ሃላፊው ከነገ ጀምሮ ጠላትን ባለበት ለመደምሰስ እና የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ዝግጅት መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡
ራስን ለማዘጋጀት እና ለማጠናከር ሲባል የወገን ሃይል በወጣባቸው አካባቢዎች ጠላት አጋጣሚውን በመጠቀም የሕዝቡን ሀብት መዝረፉን ያነሱት ሃላፊው በቀጣይ ዕድሉን ቢያገኝ በሀገሪቱ ላይ የከፋ ጥፋት እንደሚያደርስ ሕዝቡ ተረድቶ እስከመጨረሻው እንዲፋለም አሳስበዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ጦርነት ለማድረግ በተንቀሳቀሰባቸው እንደ ጉራ ወርቄ፣ ሀራ እና ዋግ አካባቢዎች አርሶ አደሩ ባደረገው ውጊያ በጠላት ላይ የፈጸሙትን ጀብዱ በሌሎች አካባቢዎችም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ነፃነት እና ክብር ያለመስዋእትነት እንደማይገኝ በመገንዘብ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የህልውና ዘመቻ የተቀናጀ ማጥቃት እንደሚካሄድና ሁሉም እንዲነሳ አሳስበዋል፡፡
ባለሃብቶችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ለሚደረገው የህልውና ዘመቻ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
መላው የአማራ ሕዝብ በአሸባሪው ትህነግ ላይ ክንዱን የሚያሳርፍበት ጊዜው አሁን መሆኑን በመረዳት በአንድነት እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.