Fana: At a Speed of Life!

ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሉዓላዊነቱን ለማስጠበቅና የሀገሩን ክብር ላለማስደፈር ቆርጦ እንዲነሳ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሉዓላዊነቱን ለማስጠበቅ በሙሉ ልቡ እንዲሰለፍና ዛሬም እንደ ጥንቱ የሀገሩን ክብር ላለማስደፈር ቆርጦ እንዲነሳ ጥሪ ቀረበ።
 
ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መንግስት ዛሬ ባስተላለፈው ሀገራዊ መልዕክት÷ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣውን የወያኔ የክህደት ኃይልና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርቧል።
 
ዛሬ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ከጠላት የመጠበቅ ታሪካዊ አደራ በእኛ ጫንቃ ላይ መውደቁን ያመለከተው መግለጫው÷ በሀገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን የሕወሐት ኃይል ከታሪክ ገጽ ለመደምሰስ በቁርጠኝነት እንድትታገሉ እናት ሀገራችሁ ጥሪ ታቀርብላችኋለች ብሏል።
 
ሀገር በመከላከል ዘመቻው ለመሳተፍ እድሜያችሁና አቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የሀገር ዘብነታችሁ የምታሳዩበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ሲልም ጥሪውን አስተላልፏል።
 
የጸጥታ ኃይሎችን በቀጥታ ለመቀላቀል ያልተቻለው የኅብረተሰብ ክፍል ከመቼም ጊዜ በላይ ወገቡን አሥሮ በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበትና የመንግሥት ሠራተኛውም በሙሉ ዐቅሙ ያለ ቢሮክራሲ ሥራውን እንዲያከናውን አሳስቧል።
 
ኢትዮጵያውያን በቃን ብለን ከተነሣን ከፊታችን የሚቆም ምንም ዓይነት ኃይል ሊኖር እንደማይችልም መግለጫው አውስቷል።
 
ውጊያው የትግራይን ሕዝብ ምሽግና መጠቀሚያ ካደረገው እኩይ ኃይል ጋር እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር አይደለም ያለው ይህ መዕልዕክት÷ የፍልሚያው ዓላማ የትግራይ ሕዝብ ብሎም መላ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ነፃ ለማውጣትና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስከበር መሆኑን አስምሮበታል።
 
ትግላችን ከአሸባሪው ጁንታ ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው ሀገራችንን ለማፈራረስና የኢትዮጵያን ህልውና ለማጨለም ከተነሡ የቅርብና የሩቅ ኃይላትና ሀገራት ጋር ጭምር መሆኑንም አስገንዝቧል።
 
የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የተኩስ አቁም አድርጎ ከወጣ በኋላ በካሀዲው ቡድን ሕጻናት ለጦርነት ሲሰለፉ፤ ርዳታ የጦርነት መሣሪያ ሲሆን፣ እናቶችና ወጣት ሴቶች ሲደፈሩ፣ የእምነት ተቋማት የጦር መለማመጃዎችና የጦር መሣሪያ መጋዘን ሲደረጉ፣ የርዳታ እህል የጫኑ መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ በጁንታው የጥፋት ተግባር ሲስተጓጎሉ በዝምታ ያለፉ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ ለመንግሥት ጥረት ተገቢውን ዋጋ መንፈጋቸው ሳያንስ፣ በርዳታ ሰበብ ጁንታውን የሚደግፍ ተግባር ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ የውጭ አካላት መኖራቸውንም አጋልጧል።
 
በአፋር ክልል በአንድ የሕክምና ተቋም የተጠለሉ ከ200 የሚበልጡ ሰዎችን ሲያርድ ፣ ከ300,000 በላይ ዜጋ ሲያፈናቅል፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እውነታው ምን እንደሆነ ለማወቅ ፍላጎት ያለው አካል ሁሉ ለመታዘብ መቻሉን አስረድቷል።
 
የአሸባሪው ጁንታ ዓላማና ግብ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንደሆነ አመራሮቹ በእብሪት የተናገሩት ሀቅ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፣ ለዓላማው መሳካትም በብዙ የውጭ ኃይሎች በመታገዝ ለበለጠ ጥፋት ምላጭ መሳብን እንደመረጠ አመልክቷል።
 
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ነቅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ፤ የጁንታው ተላላኪዎች የጥፋት ተልዕኳቸውን እንዳይፈጽሙ ሕዝቡ በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተል አሳስቧል።
 
ከዚህ ባለፈ ለሠራዊቱ የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀትና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ብርቱ ደጀን እንዲሆን፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ሕዝቡ ከሀገሩ ጎን እንዲቆም የበኩላቸን አስተዋጽኦ እንዲየሰበረክቱም ጠይቋል።
 
አሸባሪው ጁንታ ሰላማዊ ሰዎች አስመስሎ በየአካባቢው ያሠማራቸው ሰላዮችና የጥፋት ተላላኪዎችን ለመከታተልና ለማጋለጥ እንዲቻል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ዐይንና ጆሮ በመሆን ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁሟል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.