Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች ከመከላከያ ጎን እንደሚቆሙ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች መከላከያን በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆሙ አስታውቀዋል፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሃያ ወረዳና የአራት ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የህወሃት ጁንታ ቡድንን እኩይ ተግባር በመቃወምና ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በሐረማያ ከተማ የድጋፍ ሠልፍ አካሂደዋል፡፡

ሠልፈኞቹ የሃገር አንድነትን ለማስጠበቅ የህይወት መስዋትነት እየከፈለ ላለው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን በተለያየ መልኩ ለመግለፅና ከጎኑ ለመቆም ያላቸውን ዝግጁነት አስታውቀዋል፡፡

በድጋፍ ሠልፉ የህውሃት ጁንታ ቡድን በትግራይ አጎራባች ክልሎች በንጹሃን እያደረሰ ያለው እኩይ ተግባር የሽብርተኝነት ተግባሩን የሚያሳይ መሆኑን በመግለጽ÷ እድሜያቸውን ለጦርነት ያልደረሱ ህፃናትን በሃሺሽ እያናወዘ ለጦርነት የሚያሰማራውን ድርጊት አጥብቀው እንደሚያወግዙትና እንደሚቃወሙት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የጁንታውን ድርጊት እንዲያወግዝና በዓለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት እንዲጠይቅ አሳስበዋል፡፡

በሐረማያ ስታዲየም በተካሄደው ሠልፍ ላይ ‹‹ ለኢትዮጰረያ አንድነት ዘብ እንቆማልን››፣ ‹‹ህውሃት የኢትዮጵያ አንድነት ፀር ነው››፣ ‹‹የህውሃት ጁንታ ቡድን የአፍራሽና የዘረፋ ጭንቅላት እንጂ የግንባታ ስነ-ልቦና የለውም››፣ ‹‹የጀግንት እንጂ የባርነት ታሪክ የለንም››፣‹‹ከህገ-መንግስታችንና ለህገ-መንግስተዊ ስርዓታችን የምንከፍለው መስዕዋትነት ምንግዜም አይሸረሸርም››፣ ‹‹ለጀግናው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ክብር ይገባል›› እና ‹‹ ኦነግ ሸኔ የህውሃት ጁንታ ተላላኪ ናት›› የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡

በዚህ ለሃገር መከላከያ ሠራዊት በተካሄደው የድጋፍ ሠልፍ ላይ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶን ጨምሮ ሌሎች የዞኑና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በዚሁ ወቅት ባስተለለፉት መልዕክት÷ አሸባሪው የህውሃት ቡድን ሃገር ለማፍረስ የጀመረውን ጥረት እንዳይሳካ ህዝቡ ከመከላከያ ጎን በመሆን መሰለፍ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

የህውሃትን የሽብር ቡድን ከማውገዝ ባለፈም እኩይ ተግባሩን ለማስቆም ፈፅሞ ለመደምሰስ በአንድነት መቆምና አካባቢን በንቃት መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሁሴን÷ ለመከላከያ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

በድጋፍ ሠልፉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን÷ ሠልፉም በሠላም ተጠናቋል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.