Fana: At a Speed of Life!

የጸጥታ ሃይሎች በህወሓት ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመፈጸም ድል እያስመዘገቡ ነው-አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ መሬት ለአሸባሪው ህወሓት እሾህ መሆን ጀምሯል አሉ የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ፡፡
 
አቶ ግዛቸው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አሸባሪው ትህነግ ከጠላቶቻችን ጋር ግንባር ፈጥሮ የኢትዮጵያውያንን ልማትና እድገት ለማደናቀፍ ብሎም ሀገራችንን በመበታተን ጠላቶቻችን እንደፈለጉ የሚጫወቱባትና ሉዐላዊነታቸው ተደፍሮ የሚኖሩ ጎስቋላ ዜጎች ያሉባት ሀገር ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የውጭ ጠላቶቻችን አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያውያንን ለማዳከምና ለማፈራረስ የሚያገለግል መሳሪያችን በመሆኑ እንደግፈዋለን ብለው በአደባባይ የተናገሩለት ከመሆኑ በላይ በተግባር ተልእኮ ተቀብሎ ሀገራችንን በከፋ አዘቅት ላይ ለመጣል እየሠራ ያለ አሸባሪ ድርጅት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
 
ዋና ዳይሬክተሩ ከሰሞኑ የአሸባሪው ኦነግ ሸኔ መግለጫም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፤ በሱዳን በምንዋሰንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ወታደር አዘጋጅቶ ለመግባት ሲሰረስር እየተደመሰሰ የሚረግፈው የአሸባሪው ቀለብ ተከፋይ ሁሉ ከጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተላከ የመርዝ ስጦታ ነው ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያን ለማጥፋት የክህደት ክንዱን ያነሳው አሸባሪው ቡድን በአሁኑ ሰዓት በከፈተብን ወረራና ጦርነት ቀዳሚውን ጡንቻ ያሳረፈው የአማራ ሕዝብ ላይ ሲሆን ሕዝባችንን በማጥፋት ካልሆነ በስተቀር እረፍት እንደማያገኝ በመናገርና በተግባርም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እያደረገው ይገኛል ብለዋል፡፡
 
ሕዝባችን ለመከፋፈል እየሠራ ነው፡፡ አርሶ አደሩን ከግብርና ሥራ አፈናቅሏል፤ ሴቶችን ከባሎቻቸው ፊት ደፍሯል፤ ወጣቶችን ገድሏል፤ የመንግስትንና የህዝብንና የግለሰቦችን ሀብት እየዘረፈ ይገኛል። የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ አዋርዷል ነው ያሉት፡፡
 
የአማራ ሕዝብ ደግሞ ከሚያዋርደው እና ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚሠራ አሸባሪ ጋር ኅብረት የለኝም ብሎ ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይሎች፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፤ ፋኖና ሚሊሻ ጋር ተሰልፎ አሸባሪውን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣው ይገኛል ብለዋል አቶ ግዛቸው፡፡ “እንደተናገርነው የአማራ መሬት ለአሸባሪው ቡድን እሾህ መሆን ጀምሯል” ብለዋል።
 
ጀግኖች ታጋዮቻችን በራያ ግንባር ጦርነት ባለባቸው ሀራ፣ መቄት፣ መርሳና ወልዲያ እንዲሁም በዋግኽምራ ግንባር ጠላትን መውጫ መግቢያ እያሳጡት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
 
መርሳ ተስቦ ወደ ተጠመደለት ወጥመድ የገባው የአሸባሪው ቡድንም በሚገባው ልክ እየተመታ መርሳን ለቆ እየሸሸና በየስርቻው እየተወሸቀ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
 
በመቄት በኩል በጋይንት ግንባር የነበረው አሸባሪም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የተባበረ ክንድ እየተመታ ወጥመዳችን ውስጥ እየገባ ይገኛል ያሉት አቶ ግዛቸው÷ በዚህ ግንባር የአሸባሪው ቡድን አዋጊዎች ጭምር የወገንን በትር እየቀመሱት ሲሆን ሊዋጋበት የያዘውን መሳሪያ እንኳን ወደ ወገን ጦር የሚያዞርበት ቅጽበት አጥቶ እየተማረከ ነው ብለዋል፡፡
 
እየመጣበት ያለውን ማእበል ያውቀዋልና በላሊበላ ከተማ ተቆርጦ የገባው የአሸባሪው ቡድንም የመከፋፈል አጀንዳውን ከአፉ አውጥቶ ሳይጨርስ ጊዜያዊ መጠለያዎቹን እየለቀቀ የሚወጣበት አጥቶ በመንቆራጠጥ ላይ እንደሆነም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
 
የወገን ጦር በወሰደው እርምጃ የተጨነቀው አሸባሪው ቡድን ራሱን ለማትረፍ በየጥሻው የየአካባቢውን ገበሬ እየተመሳሰለ ወደ ሌሎች የአማራ አካባቢዎች በተናጠል ሰርጎ ለመግባት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
በዛሬና በትናትናው እለት በነበረው ውጊያም ከጠላት ጦር ከፍተኛ የሆነ መክዳትና መሸሽያ እየታየ በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከጸጥታ መዋቅራችን አልፎ ወደምንኖርባቸው ከተሞችና መንደሮች የሚገባ ከመንጋው የተነጠለ ሰርጎ ገብ ፍሰት ስለሚኖር ሁሉም የክልሉ ህዝብ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ዋ አሳስበዋል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.