Fana: At a Speed of Life!

የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ 600 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የመሰረተ ልማት ግንባታ  ተከናውኗል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች 600 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የጎርፍ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ ማከናወኑን ገልጿል።

የባለስልጣኑ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ ሥራዎች ላይ መክሯል።

በውይይቱም የዐብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የሌሎች ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ዐብይ ኮሚቴው ተቋማት በተናጠል ሲያከናውኑት የነበረውን ተግባር በማቀናጀት ስኬታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል ምክክር ማድረጉን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ  በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት አጋጥሞ የነበረውን የጎርፍ አደጋ በመገምገም ምን ተሰራ በቀጣይስ ምን መስራት ይጠበቃል የሚሉት ጉዳዮች መዳሰሳቸውንም ገልጸዋል።

በ2012 ክረምት ያጋጠመውን የጎርፍ አደጋ መነሻ በማድረግ አሁን ሊደርስ የሚችልን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አመላክተዋል።

የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር አዳነች ያሬድ፥በ2013 ክረምት ኦሮሚያ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ጨምሮ በሌሎች ሰባት ክልሎች የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ 600 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጪ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ውሏል ብለዋል።

አቢይ ኮሚቴው የጎርፍ ተጋላጭነትን የመቀነስ ስራውን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ ተቋማት የተካተቱበት እንደሆነም አስረድተዋል።

በቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራው ኅብረተሰቡን ወደተሻለ ቦታ ማስፈርን ጨምሮ ውሃን በተፋሰስ መገደብና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውም ተገልጿል።

ተጋላጭነትን ለመቀነስም በፌዴራልና በክልል መንግስታት መካከል የግድብ አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን ቅንጅታዊ አስራር እየተፈጠረ መምጣቱም በጥንካሬ ታይቷል።

በመሰረተ ልማት ግንባታ ወቅት ያጋጠሙ የወሰን ማስከበርና የበጀት ውስንነት ችግሮች በቀጣይ ትኩረት እንደሚሹም መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.