የሀገር ውስጥ ዜና

የግሉ ዘርፍ በኢንፎርሜሺን ቴክኖሎጂ መስክ የሚሰማራበት ምቹ ሁኔታ ተዘርግቷል

By Meseret Awoke

August 12, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሉ ዘርፍ በኢንፎርሜሺን ቴክኖሎጂ መስክ የሚሰማራበትን ምቹ ሁኔታ መዘርጋቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀምና የ2014 ዕቅድ ዋና ዋና ትኩረቱ ላይ ከሠራተኞቹ ጋር ተወያይቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ተቋሙ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዋና ተዋናይነት ወደ አስቻይነት ለመሸጋገር በ2013 በጀት ዓመት በርካታ ስራዎች ሰርቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትና ይህንኑ ባህል አድርጎ ለማስቀጠል ዘርፉ የሚመከለታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አዲሱ በጀት ዓመት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመዘርጋት የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በተለይም ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት ከክልሎች ጋር የተፈጠረው ትስስር ወደ ተግባር መቀየራቸውን የምንከታተልበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

እንደሃገር የኔቶርክ መዋቅሮችን ከማስተካከል ጀምሮ የተቋማትንና የማህበረሰቡን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎችም ትኩረት ከተሰጣቸው ስራዎች መካከል ናቸው።

ለዚህም የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕላት ፎርም ተዘጋጅቶ በአስር ቋንቋዎች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲደርስ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።

ይህም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንዲደርስ የታሰበ ሲሆን÷ እስከ 1ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ትልም መያዙ ነው የተነገረው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!