Fana: At a Speed of Life!

የሶሪያ ወታደሮች በአማጽያን ቁጥጥር ስር የነበረች ቁልፍ ከተማን አስለቀቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ ቢሲ) የሶሪያ መንግስት ወታደሮች በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበረች ወሳኝ ከተማን ነጻ ማውጣታቸው ተሰምቷል።

የሶሪያ ጦር በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ኢድሊብ ግዛት ባካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበረችውን ማራት አል ኑማ ከተማን ማስለቀቁን አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ 25 መንደሮች መቆጣጠራቸውን መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል።

ከተማዋን ለማስለቀቅ በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል በተደረገው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ወደ ወደ ቱርክ ድንበር ሸሽተዋል ተብሏል።

በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ 147 የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች እና የ151 ታጣቂዎች ህይወት ማለፉ ነው የተነገረው።

የሶሪያ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል አሊ ሜይሃውብ በሰጡት መግለጫ፥ በኢድሊብ እና አካባቢዋ የሚንቀሳቀሱ አማጽያንን በዘላቂነት ለማስወገድ የተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኢድሊብ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱት እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው የሶሪያ አማጽያን የመጨረሻዋ ጠንካራ ይዞታ መሆኗ ይነገራል።

ምንጭ፦ www.france24.com

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.