የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ዶ/ር ሊያ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከሁሉም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በቻይና የተከሰተው እና አሁን ላይ በተለያዩ ሀገራት የታየው የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚደረገው የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።
በዚህም የመንገደኞች የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች በሁሉም ስፍራዎች መተከላቸውን እና ይህም ወደ ኢትዮዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በመሳሪያው እያለፉ የሰውነታቸው የሙቀት መጠን እንዲለካ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከቻይና እና ሌሎች ቫይረሱ ከታየባቸው ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን ደግሞ እያንዳንዳቸው በየግል የሰውነት ሙቀት ልኬት እና ስለ ራሳቸው መረጃ እና ስለሚሰማቸው ስሜት ቅፅ እንዲሞሉ እየተደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ቅፅ የሞሉ ሰዎችም ምንም እንኳ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የትኩሳት እና የሳል ምልክት ባይታይባቸውም በሞሉት ቅፅ መሰረት ወደሚኖሩበት አካባቢ በመሄድ በየቀኑ የህክምና ክትትል እየተደረገባቸው ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
ዶክተር ሊያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፋና 90 ጋር በነበራቸው ቆይታም፥ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል በዓለም አቀፉም በሀገር ውስጥ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በኩል የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የሙቀት መጠናቸው እየተለካ እንዲያልፉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለየት ያለ የሙቀት ልኬት የተገኘባቸው መንገደኞች ከተገኙም ለብቻቸው የሚቆዩበት በቦሌ ጨፋ እስከ 30 ሰው የሚይዝ ማቆያ ማዕከል መዘጋጀቱን እና ሌላ ተጨማሪ ቦታ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ እና በሀገር ውስጥ ምርመራ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ አራት ኢትዮጵያውያን ለብቻቸው ተለይተው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የሳል እና የትኩሳት ምልክት የታየባቸው ሁለት ብቻ ናቸው፤ ሁለቱ አብረው ስለመጡ ብቻ አብረው እንዲለዩ ተደርጓልም ነው ያሉት ዶክተር ሊያ።
ምልክት የታየባቸው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ እየጠፋላቸው መሆኑን ጠቅሰው፥ ለተጨማሪ ምርመራ ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን እና የማረጋገጫ ምርመራው በሁለት ቀናት ውስጥ እንደሚደርስም አስረድተዋል።
ምርመራውን በሀገር ውስጥ በቀጣይ ሳምንት ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑንም ነው ዶክተር ሊያ አክለው የገለፁት።
ለባለሙያዎችም ከቅድመ ጥንቃቄ ጀምሮ ቫይረሱን መከላከል እና ማከም ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር እና ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው ያሉት ዶክተር ሊያ፥ ሌሎች ግብአት የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም አውስተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ቫይረስ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ እንደተከሰተ ማስታወቁ ይታወሳል።
ቫይረሱ በቻይና ውሃን ከተማ ይከሰት እንጂ እስከ ትናንት በወጡ መረጃዎች በሀሉም የቻይና ግዛቶች እየተዛመተ መሆኑን እያመላከቱ ሲሆን፥ ከቻይና ውጭም በታይላንድ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ቬትናም፣ ኔፓል፣ ካናዳ፣ ካምቦዲያ፣ ሲሪላንካ እና ጀርመን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸው ተነግሯል።
በቻይና ብቻ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 170 የደረሰ ሲሆን፥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 7 ሺህ 711 መድረሱ ነው የተገለፀው።
በሙለታ መንገሻ