Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የለውጥ ስራዎች ፍኖተ ካርታ ማሻሻያ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የለውጥ ፍኖተ ካርታ ማሻሻያ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው።
 
በመድረኩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በሀገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መተዳደሪያ ደንብና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሊደረጉ በሚገባቸው ማሻሻያዎች ዙሪያ ምክክር እየተደረገ ይገኛል።
 
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተጣለበትን ሃላፊነት በተገቢው ሁኔታ እንዲወጣ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
ለአንድ ቀን የሚካሄደው ውይይት በሀገሪቱ በሚስተዋሉ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።
 
የውይይት መድረኩን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ አዘጋጅተውታል።
 
በመድረኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከህዝብ ተወካች ምክር ቤት፣ ከፍርድ ቤቶች፣ ከእምባ ጠባቂ ተቋም፣ ከፖሊስ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.