የአውቶብስ ተራ-መሳለሚያ-18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውቶብስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጀምሯል።
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር የጎን ስፋት እንዳለው ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም 75 ሜትር ርዝመት ያለው ወንዝ ተሻጋሪ ድልድይ ግንባታን ያካተተ ነው።
በተጨማሪም ወደ ዋናው መንገድ የሚያስገቡ 20 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት ድልድዮች እና አንድ ማሳለጫ ድልድይ እንዲሁም የድጋፍ ግንቦች አሉት ተብሏል።
የቻይናው ሬልዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያከናውን ሲሆን፥ የምህንድስና ቁጥጥር ስራው ደግሞ በዩናይትድ ኮንሰልቲንግ ይከናወናል።
ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የተመደበለት ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እንዲከናወን ባለድርሻ አካላት ለወሰን ማስከበር ስራ ትኩረት እንዲሰጡ እና አሽከርካሪዎች የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።